አሜሪካና ካናዳ ምንነቱ ያልታወቀ አዲስ በራሪ አካል መትተው ጣሉ

ምንነቱ ያልታወቀው በራሪ አካል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በሰሜን አሜሪካ የአየር ክልል ውስጥ ምንነቱ ያልታወቀ አዲስ በራሪ አካል ተመትቶ እንዲወድቅ መደረጉን የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ አረጋገጡ።

የካናዳ የአየር ክልል ጥሷል የተባለው እና ምንነቱ ያልታወቀው በራሪ አካል በሰሜን ምዕራብ ካናዳ ዩኮን አካባቢ ነው የተመታው ብሏል።

የካናዳ እና የአሜሪካ አውሮፕላኖች ተከታትለው በአሜሪካው ኤፍ-22 ተዋጊ ጄት መመታቱን ጠቅላይ ሚንስትር ትሩዶ አስረድተዋል።

ባለፈው ሳምንት ብቻ በሰሜን አሜሪካ የአየር ክልል ተመትቶ የወደቀ ሶስተኛው በራሪ አካል ሆኗል።

የአሜሪካ ጦር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የቻይናን ፊኛ መትቶ ጥሏል። አርብ ዕለትም ደግሞ ትንሽ መኪና የሚያክል ነገር አላስካ ክልል ውስጥ ተመትቷል።

ትሩዶ ቅዳሜ ዕለት ትዕዛዙን መስጠታቸውን እና በጉዳዩ ዙሪያ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር መነጋገራቸውን አረጋግጠዋል።

"የካናዳ ጦር የተመታውን ቁስ በማሰባሰብ ምርመራ ያከናውናሉ” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ምንነቱ ለጊዜው ያልተገለጸ ነገር በማዕከላዊ ዩኮን 12,000ሜ ላይ እየበረረ ነበር። ቅዳሜ ዕለት ረፋድ አካባቢ ሊደረስበት መቻሉን የመከላከያ ሚኒስትሯ አኒታ አናንድ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

"ትንሽ" እና “የሲሊንደር” ቅርጽ ያለው ነው በማለት ገልጸውታል። ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎችን ለማግኘት ስብርባሪዎችን ለማግኘት ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው ብለዋል።

አናንድ አክለውም ከአሜሪካ ድንበር 100 ማይል ርቀት ላይ መወሰዱን ገልጸው "ለሲቪል አቪዬሽን ምክንያታዊ ስጋት" ፈጥሮ ነበር ብለዋል።

ባለፈው ቅዳሜ በደቡብ ካሮላይና የባህር ዳርቻ ላይ ከተመታው ያነሰ ይመስላል ብለዋል። 60 ሜትር ቁመት ካለውና የቻይና የስለላ ፊኛ እንደሆነ ከተጠረጠረው ያነሰ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ ቀደም ብለው በትዊተር ገጻቸው ላይ ለአሜሪካ እና ለካናዳ የአየር ክልልን የሚከላከለውን እና ተልዕኮውን ለሚመራው የሰሜን አሜሪካ የኤሮስፔስ መከላከያ ኮማንድ (ኖራድ) ምስጋና አቅርበዋል።

ኋይት ሃውስ በበኩሉ ምንነቱ ያልታወቀው በራሪ አካል "ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ" ክትትል ተደርጎበታል ብሏል።

“ከብዙ ጥንቃቄ እና በሠራዊታቸው ጥቆማ ፕሬዝዳንት ባይደን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ እንዲመታ ፈቅደዋል” ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

መሪዎቹ ስለ በራሪው ዓካል ዓላማ እና ከየት እንደመጣ ተጨማሪ ዝርዝር ጉዳዮችን ለማወቅ ስብርባሪውን መልሶ ማግኘት ጠቃሚ ስለመሆኑንም ተወያይተዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስቴር መትቶ ለማውረድ ስለነበረው ተልዕኮ ተጨማሪ መረጃ ሲሰጥ፣ ሁለት ኤፍ-22 ጄቶች አንከሬጅ አላስካ ከሚገኝ የጦር ሰፈር ተነስተው በኤይም 9X ሚሳኤል መተውታል ብለዋል።

የፔንታጎን ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄኔራል ፓት ራይደር አክለውም ኤፍቢአይ ከካናዳ ፖሊስ ጋር “በቅርብ ይሠራል” ብለዋል።

አሁኑ ይህ በራሪ አካል በሰሜን አሜሪካ የታየው ቻይናዊ ለሰለላ ሳትጠቀምበት አትቀርም ተብሎ የተገመተው ፊኛ በአሜሪካ ከተመታ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።

አርብ ዕለትም በፕሬዝዳንት ባይደን ትዕዛዝ ሌላ ምንነቱ ያልተገለጸ ነገር በአላስካ ሰማይ ላይ ተከታትሎ እንዲወድቅ ተደርጓል።

ጦሩ ባወጣው አጭር መግለጫ የአላስካ ብሔራዊ ዘብን ጨምሮ የአሜሪካ ወታደሮች አርብ የተመታውን ነገር ስብርባሪ በባህር የመፈለግ ሥራ እያከናወኑ ነው ብሏል።

ስለ ነገሩ አቅም፣ አላማ ወይም አመጣጥ ምንም ተጨማሪ ዝርዝር እንደሌለው አስታውቋል። ኤፍቢአይ በአላስካ ዴድሆርስ ከተማ አቅራቢያ በፍለጋው ዙሪያ እገዛ እያደረገ መሆኑን አረጋግጧል።