ተዋናይ ጆኒ ዴፕ የቀድሞ ሚስቱን በስም ማጥፋት ከስሶ 15 ሚሊዮን ዶላር ረታ

ተዋናይ ጆኒ ዴፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ከሰሞኑ የማኅበራዊ ሚዲያውና የትላልቅ ዜና አውታሮች መነጋገርያ የነበሩት የተዋናይ ጆኒ ዴፕ እና የቀድሞ ሚስቱ አምበር ኸርድ የችሎት ክርክር ተቋጭቷል።

የሁለቱን የሆሊዉድ ሰዎች ክስ ለማየት የተቀመጠው ችሎት ጆኒ ዴፕ በቀድሞ ሚስቱ ስሙ ጠፍቷልና 15 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ይገባዋል ብሏል።

አምበር ኸርድ ደግሞ በዴፕ ጠበቃ ስሟ በመጥፋቱ 2 ሚሊዮን ዶላር ካሳ አግኝታለች።

ሁለቱ የሆሊዉድ ፈርጦች በፈረንጆቹ 2017 ነበር ፍቺ የፈፀሙት። 

ፌርፋክስ በተሰኘችው የቨርጂኒያ ክፍለ ግዛት የተሰየመው ችሎት ለስድስት ሳምንታት የሁለቱን ክርክር ሲያደምጥ ቆይቷል።

አሜሪካዊያን ከዩክሬን ጦርነትና ውርጃን ከሚከለክለው ውሳኔ በላይ በቀድሞ ባልና ሚስት ወሬ ተጠምደው ቆይተዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲተላለፍ የነበረው የፍርድ ቤት ክርክር በቢሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች ታይቷል።

ጉዳዩን የተመለከቱ የዳኝነት አባላት ለበርካታ ሰዓታት ከመከሩ በኋላ ነው ረቡዕ ዕለት በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን ዜና ያወጁት።

አምበር ኸርድ ስለትዳሯ ያወራችው “ሐሰት ነው”፤ ይህንን ያደረገችውም “ሆነ ብላ” ነው ብሏል ችሎቱ።

በሌላ በኩል በጆኒ ዴፕ ጠበቃ ስሟ ጠፍቷል የተባለችው አምበር ኸርድ 2 ሚሊዮን ካሳ ተውስኖላታል።

ሰባት አባላት ያሉት ችሎት ውሳኔውን ሲያሰማ “ጆኒ፣ ጆኒ” በማለት ከችሎቱ ውጪ ደስታቸውን የሚገልፁ ሰዎች ድምፅ ይሰማ ነበር።

ጆኒ ዴፕ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስማት ፍርድ ቤት መገኘት አልቻለም ሲሉ ጠበቃው አስረድተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፍርድ ቤት ቀርቦ በጠበቃው በኩል ለሳምንታት ሲከራከር የነበረው ጆኒ ዴፕ፣ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከእንግሊዛዊ ሙዚቀኛ ጓደኛው ጋር ጊታር ሲመታ ታይቷል።

ከውሳኔው በኋላ መግለጫ ያወጣው ዴፕ “ችሎቱ ሕይወቴን መልሶ ሰጥቶኛል። የምር ክብር ተሰምቶኛል” ብሏል።

አክሎም “እውነት መቼም አትሞትም” ሲል መግለጫውን ቋጭቷል።

የፌርፋክስ ሰርኪዩት ፍርድ ቤት ዳኞች ጆኒ ዴፕ የተበየነለት 15 ሚሊዮን ዶላር ወደ 10.4 ሚሊዮን ዝቅ እንዲል መወሰናቸው ተሰምቷል።

ውሳኔው ሲነበብ በሐዘን ስሜት ፊቷ ጨልሞ ስታደምጥ የነበረችው ተዋናይት አምበር ኸርድ “ልቤ ተሰብሯል” ብላለች።

“ችሎቱ ያቀረብኩትን ማስረጃ ከግምት አላስገባም” ብላለች አምበር ከውሳኔው በኋላ ባወጣችው መግለጫ።

“የበለጠ ያበሳጨኝ ይህ ውሳኔ ለሌሎች ሴቶች ምን ማለት ነው የሚለውን ሳስብ ነው። ወደኋላ እንደ መጓዝ ነው። በድፍረት አደባባይ ወጥተው የሚናገሩ ሴቶች እንዲያፍሩ ወደሚደረጉበት ዘመን እንደመመለስ ነው።”

የአምበር ኸርድ ቃል አቀባይ ይግባኝ እንደሚጠይቁ አሳውቋል።

የዕለተ ረቡዕ ውሳኔ ለጆኒ ዴፕ ትልቅ ዜና ነው።

ከሁለት ዓመት በፊት የብሪታኒያው ጋዜጣ 'ዘ ሰን' ጆኒ ዴፕ “ሚስቱን የሚማታ” ነው ሲል አስነብቦ ነበር።

ነገር ግን ጆኒ ዴፕ የቀድሞ ሚስቱን የከሰሳት 'ዋሺንግተን ፖስት' በተሰኘው ጋዜጣ ላይ ስሜን አብጠልጥላለች ብሎ ነው።

ዴፕ ስሜ በመጥፋቱ 50 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ይገባኛል ሲል ነው የከሰሰው።

ምንም እንኳ አምበር “የቤት ውስጥ ጥቃትን የምወክል ታዋቂ ሴት” በሚል ባሳተመችው ፅሑፍ የጆኒ ዴፕን ስም ባትጠቅስም ዴፕ ግን ይህ ፅሑፍ ለሥራዬ እንቅፋት ሆኖብኛል ብሏል።

አምበር ኸርድ ክሱ ከደረሳት በኋላ በተራዋ 100 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ይገባኛል ስትል ከስሳለች።

ሁለቱም መቀመጫቸው ካሊፎርኒያ ይሁን እንጂ ችሎቱ የተሰየመው የዋሺንግተን ፖስት መሥሪያ ቤት በሚገኝበት ቨርጂኒያ ነው።

ዴፕና አምበር 'ዘ ራም ዳያሪ' የተሰኘውን ፊልም በመሥራት ላይ ሳሉ ነበር የተገናኙት።

በፈረንጆቹ 2011 የፍቅር ግንኙነት የጀመሩት ጥንዶቹ በ2015 ነበር ትዳር የመሠረቱት።