ኮሜዲያን ክሪስ ሮክን በጥፊ የተማታው ዊል ስሚዝ ከኦስካር ለ10 ዓመታት ታገደ

ዊል ስሚዝ ኮሜዲያን ክሪስ ሮክን መድረክ ላይ በጥፊ ሲማታ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በ94ኛው የኦስካር ሽልማት ላይ ኮሜዲያን ክሪስ ሮክን በጥፊ የተማታው ዊል ስሚዝ ከኦስካር እና ከሌሎች የአካዳሚው ቋሚ መርሐ ግብሮች ለቀጣዮቹ 10 አመታት ታገደ።

አካዳሚው ባወጣው መግለጫ የዘንድሮ የኦስካር መርሐ ግብር ስሚዝ በመድረክ ላይ ባሳየው ያልተገባ ድርጊት ተሸፍኗል ብሏል።

ቀደም ብሎ ስሚዝ ለፈጸመው ድርጊት ይቅርታ ጠይቆ ከአካዳሚው ሥራውን መልቀቁ የሚታወስ ነው። በዚህም ምክንያት ከዚህ በኋላ ስሚዝ ለኦስካር እጩዎች ድምጽ መስጠት አይችልም።

ሮክ 'አሎፔሺያ' በተሰኘ ጸጉርን በሚያረግፍ ችግር የተጠቃቸው እና ጸጉሯን የተላጨችውን የዊል ስሚዝ ባለቤት ላይ በመቀለዱ ነበር ተዋናዩ ድርጊቱን የፈጸመው።

ይህ ከሆነ አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜም ስሚዝ "ኪንግ ሪቻርድ" በተኘው ፊልም የምርጥ ተዋናይነት ሽልማት ወስዷል።

የሽልማት ሥነ ሥርዓቱን የሚያዘጋጀው 'የሞሽን ፒክቸር አርትስ ኤንድ ሳይንስ' አካዳሚ ትላንት [አርብ] ዊል ስሚዝ በፈፀመው ድርጊት ላይ ሊወስድ ስለሚገባው እርምጃ በበይነ መረብ ተወያይቷል።

ከውይይቱ በኋላ አካዳሚው ባወጣው መግለጫ ስሚዝን ከኦስካር የማገድ ውሳኔ መድረክ ላይ ዝግጅት የሚያቀርቡ ሰዎችን እና እንግዶችን ለመጠበቅ እና "በአካዳሚው ላይ ያለውን እምነት ለመመለስ" ያለመ ነው ብሏል።

አካዳሚው ይህ ድርጊት በተፈጸመበት ወቅት ለጉዳዩ በአግባቡ ምላሽ ባለመስጠቱ ይቅርታ ጠይቋል። "ከዚህ በፊት ታይቶ ለማይታወቅ እንዲህ ዓይነት ነገር በቂ ዝግጅት አላደረኩም ነበር" ሲልም ገልጿል።

ሮክ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ተረጋግቶ ነገሩን ለማሳለፍ ያደረገው ጥረት የሚመሰገን ነውም ብሏል።

በፊልም አካዳሚው የተቀመጡት የሥነ ምግባር ጥሰቶች በርካታ የቅጣት አማራጮችን ያካተቱ ሲሆን በኦስካር የሽልማት መርሐ ግብር እንዳይታደም ማገድ፣ እጩ እንዳይሆን ማድረግ እና ያሸነፈውን ኦስካር መልሶ መንጠቅን ያካትታል።

በኦስካር ሽልማት ታሪክ የተሰጠ ሽልማት የተነጠቀው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን እንደ አውሮፓውያኑ በ1969 "ያንግ አሜሪካን" የተሰኘ ፊቸር ፊልም የምርጥ ዶክመንተሪን ዘርፍ ሽልማቱን ከወሰደ በኋላ መስፈርቱን አላሟላም በሚል የተሰረዘ ነው።

ሆኖም የአካዳሚው አስተዳዳሪ የቦርድ አባል የሆነው ተዋናይ ዊኦፒ ጎልድበርግ ስሚዝ ለፈጸመው ድርጊት ቅጣት እንደሚጠብቀው ገልጾ፤ ሽልማቱን ግን መልሰን አንወስድም ብሎ ነበር።

ከአካዳሚው እግድ በተጨማሪም ሶኒ እና ኔትፍሊክስ ከዊልስሚዝ ጋር የጀመሯቸውን ፕሮጀክቶች አቁመዋል።

ከዚህ ድርጊት በኋላ የኮሜዲ ትርኢት ጉዞ እያደረገ ያለው ሮክ ስለዚያ ምሽት ክስተት በይፋ አስተያየት አልሰጠም።

"አሁንም ድረስ ምን እንደተፈጠረ እያሰብኩ ነው" ያለው ሮክ አንድ ቀን ስለጉዳዩ እናገራለው ሲል በአንድ መድረክ ላይ ለአድናቂዎቹ ተናግሯል።