ታዋቂው ተዋናይ ጆኒ ዴፕ የቀድሞ ባለቤቱን ይደበድባት ነበር መባሉ ፍፁም ሃሰት ነው አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታዋቂው የፊልም ተዋናይ ጆኒ ዴፕ የቀድሞ ባለቤቱን አምበር ሄርድን ይደበድባት ነበር መባሉ ፍፁም ሃሰት መሆኑን ጠበቆቹ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት አስረድተዋል።
ተዋናዩ ሰን የተባለውን ጋዜጣ አሳታሚ ኒውስ ግሩፕ ኒውስፔፐርስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዳን ውተንንም ከሁለት አመት በፊት "ሚስቱን ደብዳቢ" ብሎ ላወጣው ፅሁፍም ከስሷል።
ተዋናዩ ባለቤቱን በጭራሽ ይደበድባት እንዳልነበር ቢያስረዳም የአሳታሚው ጠበቆች በበኩላቸው "ሚስት ደብዳቢ" የሚለው አገላለፅ የተዋናዩ ትክክለኛ ጠባይ መገለጫ ነው በማለት ፀንተዋል። ተዋናዩ እንዲሁም የቀድሞ ባለቤቱ አምበር በትናንትናው ዕለት ለንደን የሚገኝ ፍርድ ቤትም ቀርበው ነበር።
የተዋናዩ ጠበቃ ዴቪድ ሸርቦርን ደንበኛቸውንም ወክለው ባቀረቡት የፅሁፍ መከራከሪያ "የጋዜጣው ፅሁፍ የቀድሞ ባለቤቱን ይደበድባት እንደነበርና ለህይወቷም መፍራቷንም በመጥቀስ ደንበኛዬን ወንጅለውታል። ይህ ፍፁም ሃሰት ነው፣ የተዋናዩን ስም አጠልሽቶታል፤ ስሙንም አጥፍተውታል" ያሉ ሲሆን አክለውም
"ጆኒ ዴፕ የቀድሞ ባለቤቱን ጥቃት ፈፅሞባታል መባሉ ትክክል አይደለም። በአንፃራዊው የቀድሞ ባለቤቱ እሱ ላይ ጥቃት ትፈፅም ነበር" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኤንጂኤን ጠበቃ ሳሻ ዋስ በበኩላቸው "ተዋናዩ የሚያፀይፍ ባህርይ ነበረው" ያሉ ሲሆን "በተደጋጋሚም ጠበኛነቱን አሳይቷል" በማለትም ተከራክረዋል። ተዋናዩ ግን በፍፁም በማለት ክዷል።
ፍርድ ቤቱም ላይ ተዋናዩ ሳያውቀው የተቀረፀ አንድ ቪዲዮም ታይቷል። በቪዲዮውም ላይ ተዋናዩ ከጫፍ ጫፍ ሲመላለስና፣ ሲሳደብ እንዲሁም ቁምሳጥን በእርግጫ ሲል ታይቷል።
ጠበቃ ሳሻም በዚህ ቪዲዮ ላይ ጠበኛነቱን አሳይቶ እንደሆነ አሳይቶ እንደሆነ በተጠየቀበት ወቅት "በቁምሳጥኖቹ ላይ አዎ፤ የተናደድኩበት ወቅት ነው" ብሏል። ተዋናዩ የቀድሞ ባለቤቱንም በቦክስ ትደብድበው እንደነበርና የቮድካ ጠርሙስም ወርውራበት እንደምታውቅ አስረድቷል።
አሳታሚ ድርጅቱ ፍርድ ቤቱ ክሱን ውድቅ እንዲያደርገውም ለማድረግ ሞክሯል።
በሰን ላይ የወጣው ፅሁፍ የቀድሞ ባለቤቱን ዋቢ ያደረገ ነው። በፓይሬትስ ኦፍ ዘ ካሪቢያን የሚታወቀው ተዋናይና ባለቤቱ ለሁለት አመታትም ተጋብተው ነበር።
የተዋናዩ የቀድሞ ባለቤቶች ዊኖና ራይደርና ቫኔሳ ፓራዲዝ ምስክርነታቸውንም ይሰጣሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ የፍርድ ሂደቱም ሶስት ሳምንታት እንደሚፈጅ ተገልጿል። ጆኒ ዴፕ በፊልሙ አለም በርካታ ሽልማቶችን ያሸነፈ ሲሆን ለኦስካርና ባፍታም ታጭቶ ነበር።












