በአሜሪካ ኬንተኪ ግዛት በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ አምስት ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአሜሪካዋ የኬንተኪ ግዛት ሉዊስቪል ከተማ ውስጥ በጦር መሳሪያ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸውን ፖሊስ አረጋገጠ።
በጥቃቱ ከተገደሉት በተጨማሪ አንድ የፖሊስ መኮንን ጨምሮ ስድስት ሰዎች የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተገልጿል።
የአካባቢው ነዋሪዎችም ጥቃቱ ከተፈጸመበት ስፍራ እንዲርቁ በፖሊስ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
ከጥቃቱ ስፍራ በወጣ ቪዲዮ ላይ በካባዱ የታጠቁ ፖሊሶች የንግድ ተቋም የሆነን አካባቢ በመከለል ከእንቅስቃሴ ውጪ ሲያደርጉ ታይቷል።
የሉዊስቪል ፖሊስ በሰጠው አጭር ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ ጥቃቱን ተከትሎ ወደ አካባቢው የተሰማሩ የፖሊስ መኮንኖች ተኩስ እንደገጠማቸው አመልክቷል።
ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ መሞቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ለሞቱ ምክንያት ምን እንደሆነ ግን ግልጽ አልተደረገም።

የፎቶው ባለመብት, cbs
ከጥቃቱ ስፍራ የተላለፉ የዜና ምስሎች በርካታ ፖሊሶች መሰማራታቸውን፣ መስታወቶች መሰባበራቸውን እንዲሁም አገልግሎት ላይ የዋሉ የህክምና መገልገያዎችን አሳይተዋል።
የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ጥቃቱን ተከትሎ በስፍራው በመገኘት የአካባቢውን ፖሊሶች እያገዘ መሆኑን በትዊተር ገጹ ላይ አመልክቷል።
የኬንተኪ አገረ ገዢ ኤንዲ ቤሺር፣ የጦር መሳሪያ ጥቃቱ ወደ ተፈጸመበት ስፍራ እያመሩ መሆናቸውን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ጨምረውም “እባካችሁ በጥቃቱ ለተጎዱ ለሁሉም ቤተሰቦች እና ለሉዊስቪል ከተማ ጸልዩ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የከተማዋ ከንቲባ ክሬግ ግሪንበርግም ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከስፍራው ደርሰዋል።
ይህ ጥቃት የተፈጸመው በሉዊስቪል ከተማ ማዕከላዊ ክፍል ውስጥ ስታዲየም እና የስብሰባ ማዕከል በሚገኝበት ታዋቂ ቦታ ላይ ነው ተብሏል።












