የተተቹት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የቤተሰባቸውን የምግብ ወጪ እንደሚሸፍኑ ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት ለቤተሰቦቻቸው የምግብ ወጪ ከራሳቸው ኪስ እንደሚከፍሉ አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በጣም የተንደላቀቀ ኑሮ እንደሚኖሩና ለጊዜው መኖሪያቸው ባደረጉት ግቢ ውስጥ ብዙ ወጪ እንደሚያወጡ የሚገልጽ ዘገባ ተሠርቶ ነበር።
ይህንን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየወሩ 26 ሺህ 400 ዶላር ከግብር ከፋዮች ኪስ ተቆርጦ እንደሚሰጣቸውና ከዚህም ውስጥ 7400 ዶላር ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው የምግብ ፍጆታ እንደሚውል ገልጸዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው በፊት ሚሊየነር የነበሩት ናፍታሊ ቤኔት ሕጉ ከሚፈቅድላቸው ውጪ ምንም ዓይነት ተግባር እንዳልፈጸሙ በመግለጽ ይከራከራሉ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ባወጣው መግለጫ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በየወሩ 84 ሺ 300 ዶላር ያወጡ እንደነበር በመግለጽ፣ ከአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ወጪ ጋር ሲነጻጸር እንደውም በሦስት እጥፍ እንደሚበልጥ አስታውቋል።
ቤንያሚኒን ኔታንያሁ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በጣም ውድ የሆኑ ምግብ ቤቶች ውስጥ ይመገቡ እንደነበረና ሌላው ቀርቶ ጸጉራቸውን የሚስተካከሉት እንኳን እጅግ በጣም ውድ በሆኑ ቦታዎች እንደሆነ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በስፋት ይዘግቡ ነበር።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መንግሥት ከሚያዘጋጅላቸው መኖሪያ ይልቅ ቴል አቪቭ የሚገኘው የግል መኖሪያ ቤታቸውን እንደ ቢሮነት እየተገለገሉበት ቢሆንም ያለአግባብ ወጪ እያወጡ ነው ከሚል ክስ ግን ማምለጥ አልቻሉም ።
ባሳለፍነው ሳምንት ቻናል 13 ቲቪ የተባለው ጣቢያ በሠራው ዘገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለግል ሠራተኞቻቸው ክፍያ፣ ለጽዳት እንዲሁም ለምግብ በሚል ከፍተኛ የመንግሥት ገንዘብ እንደሚያባክኑ ዘግቦ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን በፌስቡክ ገጻቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት መሰል ያለአግባብ የሚወጣ የግብር ከፋዮች ገንዘብ በእሳቸው አስተዳደር ዘመን በእጅጉ መቀነሱንና የሚቀርብባቸውም ክስ እንዳሳቃቸው ገልጸዋል።
አክለውም ምንም እንኳን መንግሥት ምግብ አብሳይ የሚቀጥርላቸው ቢሆንም ስድስት አባላት ያለው ቤተሰባቸው ግን የግል አብሳይ እንዳልቀጠረና በአማራጭነት ከሬስቶራንቶች ምግብ እንደሚያስመጡ አብራርተዋል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ቤተሰብ ለምግብ ብቻ በየወሩ 11 ሺህ 100 ዶላር ያወጣ እንደነበርም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔፍታሊ ቤኔት ትናንት ረቡዕ ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት ደግሞ የቀረበባቸውን ክስ ባይቀበሉትም እንኳን ከዚህ በኋላ የቤተሰባቸውን ሙሉ የምግብ ወጪ እራሳቸው እንደሚሸፍኑ አስታውቀዋል።
"ምንም እንኳን እኔና ቤተሰቦቼ ከሕግ ውጪ የሆነ ምንም ነገር ባናደርግም በሕዝቡ ዘንድ የተፈጠረውን ቅሬታ እረዳለሁ። ከዚህ በኋላ የቤተሰቦቼን ሙሉ የምግብ ወጪ ከኪሴ ለመክፈል መወሰኔን በስሬ ለሚገኙና ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ አስረድቻለው" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
አክለውም "ወደዚህ ኃላፊነት የመጣሁት ክብር አልያም ገንዘብ ለማግኘት ብዬ አይደለም። እዚህ ያለሁት የእስራኤልን ዜጎች ለማገልገል ነው'' ብለዋል።
ኔፍታሊ ቤኔት ወደ ፖለቲካው ዓለም ከመግባታቸው በፊት ሁለት የቴክኖሎጂ ድርጅቶቻቸውን በ250 ሚሊየን ዶላር ሸጠው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ ደግሞ በአጠቃላይ በየወሩ መንግሥት የሚከፍላቸው ደሞዝ 16 ሺህ 500 ዶላር ነው። ይህ ደግሞ በአማካይ የእስራኤል ዜጎች በየወሩ ከሚያገኙት ደሞዝ አንጻር ከፍተኛ የሚባል አይደለም።












