ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቀድሞ የቡርኪናፋሶ ፕሬዚዳንት በቶማስ ሳንካራ ግድያ የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደባቸው
በቡርኪናፋሶ የሚገኘው ወታደራዊ ፍርድ ቤት በቀድሞው ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓዎሬ ላይ በቶማስ ሳንካራ ግድያ ላይ እጃቸው አለበት በሚል የእድሜ ልክ እስራት ፈርዶባቸዋል።
አብዮተኛ መሪ የሚባለው የ37 አመቱ ቶማስ ሳንካራ ኮምፓወሬን ወደ ስልጣን ባመጣው መፈንቅለ መንግሥት ከሌሎች 12 ሰዎች ጋር በጥይት የተገደለው በአውሮፖውያኑ 1987 ነው።
ኮምፓዎሬና ቶማስ ሳንካራ የቅርብ ጓደኞች የነበሩ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 1983ም በጋራ ስልጣን ተቆጣጠሩ።
ቶማስ ሳንካራ በፀረ-ኢምፔሪያሊስት አቋሙና በአልበገር ባይነቱ በበርካታ አፍሪካውያን ዘንድ እንደ ጀግና ይታያል።
የቶማስ ሳንካራን መገደል ተከትሎ ኮምፓዎሬ ለ27 ዓመታት ያህል በስልጣን ላይ የቆዩ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2014ም ከስልጣን እንዲወርዱ ተደርገዋል።
በቀጣዩ አመትም የእስር ትዕዛዝ ወጣባቸው።
በአውሮፓውያኑ 2014 በህዝብ ተቃውሞ ከስልጣን ከተወገዱም በኋላ በግዞት በአይቮሪ ኮስት የሚኖሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የአይቮሪኮስት ዜጋ ናቸው።
በግዞት ላይ የሚገኙት ኮምፓወሬ ባልቀረቡበት ችሎትም ነው ብያኔው የተላለፈባቸው።
ቶማስ ሳንካራን በመግደል ወንጀል ሌሎች 13 ሰዎች የተፈረደባቸው ሲሆን ከነዚህም መካከል የቀድሞ የደህንነት ኃላፊው ሃያሲንቴ ካፋንዶ እንዲሁ በሌሉበት የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል።
ሁለቱም ክሱን ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በ 1987 መፈንቅለ መንግስት ወቅት ከሠራዊቱ አዛዦች አንዱ የነበሩትና ዋነኛው ተከሳሽ ጊልበርት ዳይንደርሬ በችሎቱ ላይ ተገኝተው የነበረ ሲሆን የእድሜ ልክ እስራትም ተፈርዶባቸዋል።
በአውሮፓውያኑ 2015 ለተደረገው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የ20 አመት እስር ተፈርዶባቸው በእስር ላይ ይገኛሉ።
ቡርኪናፋሶን ይመራ የነበረውና የማርክሲስ ርዕዮተ ዓለምን ይከተል የነበረው ቶማስ ሳንካራ በዋና ከተማዋ ዋጋዱጉ በአውሮፓውያኑ 1987 በታጠቁ ሰዎች ነበር የተገደለው።
አብዮተኛው መሪ ሳንካራ ጭቆናን አጥብቀው የሚጠየፍ፣ ለድሆች፣ ሴቶችን ጨምሮ መዋቅራዊ ጭቆና አለባቸው ብሎ ለሚያምነውና ለህዝቦች እኩልነትን የሚያቀነቅን፣ ቅኝ ገዥዎችንና ኢምፔሪያሊዝምን የሚቃወም፣ ህዝብ ለመብቱ እንዲነሳ ታግሎ ያታገለ እንደነበሩ ታሪክ ይዘክረዋል።
ይኼም ብቻ ሳይሆን ምዕራባውያን በብድር ስም አፍሪካውያንን ይበዘብዛሉ በማለት የአለም ባንክና የአለም ገንዘብ ድርጅትን አጥብቶ በመተቸቱ በምዕራባውያኑ ጥርስ ውስጥ እንዲገባ ምክንያት ሆኗል።