ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአዲስ አበባ ታግዶ የነበረው መሬት ነክ አገልግሎት መጀመሩ ተገለጸ
በአዲስ አበባ በጊዜያዊነት ታግዶ የነበረው መሬት ነክ አገልግሎት መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዛሬው ዕለት አስታውቋል።
የከተማ አስተዳደሩ በባለፈው አመት መጨረሻ ነሐሴ ጀምሮ መሬት ነክ አገልግሎትን በጊዜያዊነት አግዶ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት እግዱ ተነስቶ አገልግሎቱም በየክፍለ ከተማው ማግኘት እንደሚቻል በማኅበራዊ ትስስር ገጹ በበዛሬው ዕለት ጥር 17፣ 2014 ዓ.ም አስታውቋል።
ህጋዊ ሰነድ ላላቸው ይዞታዎች ብቻ የዋስትና እዳ መመዝገብ፣ የፍርድ ቤት እና የባንክ እግድ የመመዝገብና የመሰረዝ አገልግሎት፣ በባንክ ሃራጅ፣ በፍርድ ቤት አፈፃፀም፣ የኮንደሚኒየም ቤቶች፣ በውርስ የተላለፉ ንብረቶች፣ በሪል ስቴቶች የተፈጸሙ የቤት ሽያጮች የስም ዝውውር ስራም እግድ ከተነሳላቸው አገልግሎቶች መካከል የተጠቀሱ ሲሆን አገልግሎቱም ከጥር 13፣ 2014 ዓ.ም ዕለት መጀመሩ ተገልጿል።
በተጨማሪም ለነባር ይዞታዎች የቦታ ኪራይና የቤት ግብር ተመን፣ የንብረት ግመታ፣ በይዞታ ይገባኛል ክርክር በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማስረጃ መስጠት፣ የወሰን ይመላከትልኝ /የወሰን ችካል/፣ በከተማ አስተዳደር የሚታወቅ እና ቅድሚያ የሚሰጥ የልማት ተነሺ አገልግሎት፣ የወሰን ማስከበር ተግባራትንም አገልግሎቶች ማግኘት እንደሚቻልም ተመልክቷል።
የቦታ ዝግጅት፣ የወሰን ማስከበር ተግባራት፣ በሊዝ በተላለፈ ቦታ ላይ የግንባታ ክትትል፣ የለማ መሬት በምደባ ወይም በጨረታ ማስተላለፍ፣የምትክ ኮንዶሚኒየም ቤት ለተወሰነላቸው፣ ለአመራር የሚሰጡ ኮንዶሚኒየም ቤቶች፣ ለሪል ስቴት ተጠቃሚዎች /ቤት ገዥዎች የተናጠል ካርታ/ አዲስ ካርታ አስተዳደሩ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች እንደሆኑም ተጠቅሰዋል።