ታሊባን ሴቶችን ከቴሌቪዢን ድራማዎች የሚያግድ ሕግ አወጣ

ታትሟል

ታሊባን የሚመራው የአፍጋኒስታን መንግሥት ሴቶች የቴሌቪዢን ድራማ ላይ እንዳይሳተፉ የሚያግድ ሕግ ተግባራዊ አደረገ።

ከዚህ በተጨማሪም ታሊባን ሴት የቴሌቪዢን አቅራቢዎች ፀጉራቸውን የሚሸፍን ስካርፍ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ አውጥቷል።

ታሊባን ያወጣቸው ሕጎች ግልጽ ያልሆኑ እና ለተለያዩ ትርጓሚዎች ከፍት ናቸው ተብሏል።

ታሊባን ባለፈው ሚያዚያ ወር ወደ ሥልጣን ከተመለሰ ጀምሮ አሳሪ የሆኑ ሕጎችን እያስተዋወቀ ነው።

ታሊባን ሥልጣን እንደያዘ ካስተላለፋቸው ሕጎች ቀዳሚው ሴቶችን ከትምህርት ቤት እንዲቀሩ ያገደበት ሲሆን፤ እ.ኤ.አ. ከ1990 በፊት አፍጋኒስታንን በሚያስተዳድርበት ወቅት ሴቶች ትምህርት እንዲሁም ሥራ ቦታ መሄድ አይፈቀድላቸውም ነበር።

አዲስ የወጡት የታሊባን ሕጎች በአፍጋኒስታን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የተላለፉ ሲሆን ስምንት ዋና ዋና መገለጫዎች አሏቸው።

የመጀመሪያው ከሸሪአ መርሆዎች እንዲሁም ከአፍጋን ባህል ውጪ የሆኑ ፊልሞች እንዳይተላለፉ የሚከለክል ሲሆን፤ ወንዶችም ቢሆኑ አካላቸውን በሚያሳዩ ድራማዎች ላይ እንዳይሳተፉ ታግደዋል።

ሐይማኖትን የሚሰድቡ ወይም የአፍጋን ዜጎችን ሊያስቆጡ ይችላሉ የሚባሉ ይዘቶችም እገዳው ይመለከታቸዋል። የውጪ ባህልን የሚያስተዋውቁ ፊልሞች እንዳይታዩም ታሊባን ከልክሏል።

የአፍጋን የቴሌቪዢን ጣቢያዎች ሴት መሪ ተዋናዮች የሚከውኗቸውን የውጪ አገር ድራማዎችን ማስተላለፋቸው የተለመደ ነበር።

በአፍጋኒስታን ያሉ ጋዜጠኞችን የሚወክል አንድ ማኅበር አባል የሆነው ሁጃቱላ ሙጃድዲ ለቢቢሲ እንዳለው የአዳዲሶቹ ሕጎች መውጣት ያልተጠበቀ ነው።

አንዳንዶቹ ለመተግበር የሚያስቸግሩ እና እንዲተገበሩ የሚደረግ ከሆነም የሚዲያ ተቋማት በራቸውን እንዲዘጉ ጭምር የሚያስገድዱ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግሯል።

ታሊባን ሴቶችን ከትምህርት ቤት ያገደበት ውሳኔው አፍጋኒስታንን በዓለም ግማሹ ሕዝቧን የትምህርት እድል እንዳያገኝ የከለከለች ብቸኛዋ አገር አድርጓታል።

የካቡል ከተማ ከንቲባ በበኩላቸው ለማዘጋጃ ቤቱ ሴት ሠራተኞች ሥራዎቻቸው በወንድ ሠራተኞች ሊተኩ የማይችሉ ካልሆኑ በስተቀር ቤታቸው እንዲቀመጡ ማዘዛቸው ይታወሳል።