ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሟቹ ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ እጮኛ ጀስቲን ቢበር በሳዑዲ እንዳይዘፍን ተማጸነች
በአሰቃቂ ሁኔታ ቱርክ ኢስታንቡል ውስጥ በሚገኝ የሳዑዲ ቆንስላ ውስጥ የተገደለው የጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ እጮኛ ለእውቁ ሙዚቀኛ ጀስቲን ቢበር የተማጽኖ ደብዳቤ ጻፈች።
ደብዳቤው ጀስቲን ቢበር በሚቀጥለው ወር በሳዑዲ የሚያቀርበውን የሙዚቃ ኮንሰርት እንዲሰርዝ የሚማጸን ነው።
ካናዳዊው ሙዚቀኛ ጀስቲን ቢበር በሚቀጥለው ወር በጂዳ ፎርሙላ ዋን የመኪና ውድድር ላይ ተገኝቶ ሥራዎቹን እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።
ለዚህም ነው የኻሾግጂ እጮኛ የነበረችው ቱርካዊቷ ሀቲስ ሰንጊዝ ለጀስቲን ቢበር ይፋ የተማጽኖ ደብዳቤ የጻፈችው።
"ኮንሰርቱን በመሰረዝ ለነፍሰ ገዳዩ የሳዑዲ መንግሥት ግልጽ መልዕክት እንድታስተላልፍ እፈልጋለሁ" ብላለች በዚሁ ደብዳቤዋ።
ጋዜጠኛ ኻሾግጂ የሳዑዲ መንግሥትን የሚመለከቱ የሰሉ ትችቶችን በዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ ላይ ይጽፍ የነበረ ሰው ነው። ከሳዑዲ ከመሸሹ ቀደም ብሎ ደግሞ የሳዑዲ ንጉሣዊያን ቤተሰብን ያማክር እንደነበር ይታወቃል።
ጋዜጠኛው በቱርክ ኢስታንቡል የጋብቻ ሰነድ ለማሳደስ በተገኘበት ወቅት ግን በሳዑዲ ቆንስል ውስጥ ተገድሎ ፍጹም ደብዛው እንዲጠፋ ተደርጓል።
ይህ በሚሆንበት ቅጽበት እጮኛው ከቆንስላው ደጅ የእሱን ጉዳይ ጨርሶ መውጣት እየጠበቀች ነበር።
ይህ አሰቃቂ ግድያ በፈረንጆች ጥቅምት 2018 የተፈጸመ ሲሆን ግድያው የተፈጸመበት መንገድ እጅግ ጭካኔ የተሞላበት ስለነበረ የዓለምን ትኩረት ይዞ ቆይቷል።
የጀማል አስክሬን ከሪያድ በተላኩ የነፍሰ ገዳዮች ልዩ ቡድን ምናልባትም በኬሚካል አማካኝነት ወደ ፈሳሽነት እንደተቀየረ ይገመታል።
የጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ የቀድሞ እጮኛ በዚህ ለጀስቲን ቢበር በጻፈችው ይፋ ደብዳቤ፣ "ለገዳይና ጨካኝ መንግሥት ሄደህ ባትዘፍን ደስ ይለኛል" ስትል ትማጸናለች።
የአሜሪካ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ባደረገው ምርመራ የሳዑዲው መሐመድ ቢን ሳልማን ይህን የጋዜጠኛውን አሰቃቂ ግድያ እንዲፈጸም ቀጥተኛ ፍቃድ መስጠታቸውን ደርሶበታል።
ሆኖም ልዑል አልጋ ወራሽ ቢን ሳልማን ይህን አላደረኩም ሲሉ ይከራከራሉ።
የትራምፕ አስተዳደር በወቅቱ ከሳዑዲ ጋር የቢሊዮን ዶላሮች የጦር መሣሪያ ስምምነት ያደረገ በመሆኑ በይፋ ልዑል አልጋ ወራሹን ለማውገዝ ሞራል አጥቶ ነበር።
የሳዑዲ አረቢያ ንጉሣዊ ቤተሰብ በመንግሥቱ ላይ ትችት የሚሰነዝሩ ዜጎቹን በየትኛውም የዓለም ጥግ ቢሆኑ አፍኖ የማስገደል ታሪኮች አሉት።
በሳዑዲ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች የከፉ የሚባሉ ሲሆን በተለይም በሴቶች መብት ላይ የሚደርሱ ጭቆናዎች መጠነ ሰፊ እንደሆኑ ይነገራል።
ከዚህ ቀደም ኒኪ ሚናዥ ሳዑዲ በዜጎች ላይ የምታደርሰውን ሰብአዊ መብት ጥሰት በመቃወም በጂዳ ታቀርብ የነበረውን ኮንሰርት ሰርዛለች።
ጀስቲን ቢበር ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስድ ይጠበቃል።