ተጭበርብሯል ተብሎ በተተቸው የሩስያ ምርጫ የፑቲን ፓርቲ አሸነፈ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ፓርቲ በምክር ቤት አብላጫ ድምጽ በማግኘት ምርጫውን አሸነፈ።
ምንም እንኳን ምርጫው ተጭበርብሯል ተብሎ ቢተችም በፑቲን የሚመራው ዩናይትድ ራሽያ ፓርቲ ወደ 50% ድምጽ አግኝቷል።
የፑቲን ቀንደኛ ተቺዎች በምርጫው እንዳይሳተፉ ከመታገዳቸው ባሻገር መራጮች ድምጽ እንዲሰጡ እንደተገደዱና የምርጫ ኮሮጆ ውስጥ የተጭበረበሩ ድምጾች እንደተገኙ ተገልጿል።
የሩስያ ምርጫ ኮሚሽን በበኩሉ ምርጫው ተጭበርብሯል በማሉን አስተባብሏል።
ከፑቲን ፓርቲ ጋር በዋነኛነት የተፎካከረው ኮምኒስት ፓርቲ 19% ድምጽ አግኝቷል። ስለዚህም የፑቲን ፓርቲ ከምክር ቤቱ 450 መቀመጫዎች መካከል ከሁለት ሦስተኛው በላይ የሚሆኑትን ይቆጣጠራል።
እአአ በ2016 በተካሄደው ምርጫ ፓርቲው 54% ድምጽ ነበር ያገኘው። ዘንድሮ ያገኘው ድምጽ በመጠኑም ቢሆን ቀንሷል።
ምክር ቤት ውስጥ የፑቲንን ፓርቲ ሐሳብ ከሞላ ጎደል የሚደግፈው ኮምኒስት ፓርቲ ባለፈው ምርጫ 6% ድምጽ አግኝቶ ነበር። ዘንድሮ ግን የመረጡት ሰዎች ቁጥር ከፍ ብሏል።
አሶሽየትድ ፕረስ እንደዘገበው፤ የኮምኒስት ፓርቲ መሪ ጌንዳይ ዚጋኖቭ ምርጫው በተለያዩ አይነት የማጭበርበሪያ መንገዶች የተሞላ ነበር ሲሉ ተችተዋል።
የምርጫ ኮሚሽን ኃላፊ ኤላ ፓምፊቮላ የፊታችን አርብ አጠቃላይ ውጤት ይፋ ይደረጋል ብለዋል።
ሩስያ ውስጥ ያለው ፈታኝ የኑሮ ሁኔታ እንዲሁም አስተዳደሩ በሙስና ተዘፍቋል የሚሉ ክሶች የፑቲን ደጋፊዎች ቁጥር እንዲቀንስ ማድረጋቸውን ተንታኞች ይናገራሉ።
በተለይም እስር ላይ የሚገኘው የፑቲን ተቺ አሌክሲ ናቫልኒ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።
በሌላ በኩል ፑቲን ለምዕራባውያን ጫና የማይንበረከኩ እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስቀድሙ ናቸው የሚለው አመለካከት ብዙ ሩስያውያን ፕሬዝዳንቱን እንዲደግፉ አድርጓቸዋል።
ትላንት በቴሌቭዥን የቀረቡት ፑቲን መራጩን ሕዝብ አመስግነዋል። ፓርቲያቸው ምርጫውን ያሸነፈው በነጻና ፍትሐዊ የምርጫ ሂደት እንደሆነ ያምናሉ።
የናቫንሊ ደጋፊዎች ደግሞ ምርጫውን እንደማይቀበሉት ገልጸው ተቃውሞ ጠርተዋል።
የናቫንሊ ደጋፊዎችን ጨምሮ ፑቲን ላይ የሰላ ሂስ ያሰሙ የነበሩ ተቃዋሚዎች በምርጫው እንዲሳተፉ አልተፈቀደላቸውም።
በምርጫ ሂደቱ መራጮች ላይ ጫና እንደተደረገ፣ የምርጫ ታዛቢዎች ማስፈራሪያ እንደደረሳቸው እና የምርጫ ኮሮጆ ውስጥ የተጭበረበሩ ድምጾች እንደተገኙ ተገልጿል።
መራጮች ከአንድ በላይ የድምጽ መስጫ ወረቀት ኮሮጆ ውስጥ ሲከቱ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችም ሾልከው ወጥተዋል።
እንደ መዲናዋ ሞስኮ ባሉ ከተሞች የድምጽ መስጫ ሰዓት ሲቃረብ ድምጽ የሚሰጠው በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ ነው በማሉም ጥያቄ አስነስቷል።
ሚካሂል ሎባኖቭ የተባለ የኮምኒስት ፓርቲ አባል የፑቲን ፓርቲ "እንዲህ ያለው ውጤት ሊያገኝ እንደማይችል አውቃለሁ" ሲል ትዊት አድርጓል።
ሰኪውሪቲ ኤንድ ኮኦፕሬሽን ኢን ዩሮፕ የተባለው ተቋም ምርጫውን እንዳይታዘብ በሩስያ መንግሥት እገዳ ተጥሎበታል።
ተቋሙ ከ1993 ወዲህ የሩስያን ምርጫ ሳይታዘብ ሲቀር የዘንድሮው የመጀመሪያው ነው።
የአውሮፓ ሕብረት ቃል አቀባይ ምርጫው በተገቢው ሁኔታ ቁጥጥር አልተደረገበትም ብለው ተችተዋል።
የዩናይድት ኪንግደም፣ የጀርመን እና የአሜሪካ መንግሥታትም ምርጫው ነጻና ፍትሐዊ አልነበረም ብለዋል።
ገለልተኛው እና ጎሎስ የተባለው ምርጫ ታዛቢ ቢያንስ 5,000 የተጭበረበሩ ድምጾች እንዳሉ ሪፖርት ደርሶኛል ቢልም የሩስያ መንግሥት ድርጅቱን "የውጪ ኃይሎች ተላላኪ" ሲል አጣጥሎታል።
የናቫልኒ ቃል አቀባይ ኪራ ያራምሽ "2011 ላይ እንዳደረጉት ሁሉ አሁንም ምርጫውን አጭበረበሩ" ስትል ቃሏን ሰጥታለች።
አንድ የጸጉር ቤት ሠራተኛ "ድምጽ የመስጠት ጥቅሙ አይታየኝም። እነሱ እንደሆነ ምርጫውን እንደሚያሸንፉ ቀድመው ያውቃሉ" ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።












