የጤና እክል ገጥሟቸዋል የተባሉት የጂቡቲው ፕሬዝዳንት ከፈረንሳይ ተመለሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጂቡቲው ፕሬዝደንት እስማኤል ኦማር ጉሌህ ከፈረንሳይ ወደ ጂቡቲ መመለሳቸውን ንብረትነቱ የመንግሥት የሆነው ቴሌቪዝን ጣቢያ አርቲዲ ጂቡቲ ዘገበ።
ፕሬዝደንቱ ወደ ፈረንሳይ የሄዱት የጤና እክል ገጥሟቸው ነው የሚል ጭምጭምታ ለሳምንታት ሲሰማ ነበር። ነገር ግን የጂቡቲ መንግሥት ጭምጭምታውን አጣጥሎታል።
የ73 ዓመቱ እስማኤል ኦማር ጉሌህ ፈረንሳይ ውስጥ እየታከሙ ነው የሚለውን የማኅበራዊ ሚዲያ ወሬ መንግሥት ሐሰት ነው ሲል አስተባብሎት ነበር።
ትላንት ፕሬዝደንቱ ከአውሮፕላን ሲወርዱ እንዲሁም አቀባበል ላደረጉላቸውን የመንግሥት ባለሥልጣናት ሰላምታ ሲሰጡ በብሔራዊው ቴሌቭዥን ጣቢያ ታይቷል።
እንደ አርቲዲ ጂቡቲ ዘገባ፤ ፕሬዘደንቱ ወደ ፈረንሳይ ያቀኑት ለግል ጉብኝት ነው።
ተቃዋሚ ፓርቲው ራሊ ፎር አክሽን ዴሞክራሲ ኤንድ ኢኮሎጂካል ዴቨሎፕመንት (አርኤዲዲኢ) ፕሬዝደንት እስማኤል ኦማር ጉሌህ ከሳምንት በላይ ለሆነ ጊዜ ከሕዝብ ዕይታ መጥፋታቸው አጠራጣሪ ነው ብሏል።
መሪው ከዕይታ ከመጥፋታቸው ባሻገር ስለ ጤና ሁኔታቸው ግልጽ መረጃ አለመሰጠቱንም ተቃዋሚ ፓርቲው ተችቷል።
እአአ ከ1999 አንስቶ ሥልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዝደንቱ ለአምስተኛ ጊዜ የተመረጡት ባለፈው ግንቦት ወር ላይ እንደነበር ይታወሳል።
ተቃዋሚዎች ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ተቀባይነት የለውም ብለውም ነበር።
ጂቡቲ ለወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ ዋነኛ መተላለፊያ ስትሆን ከወደብ ኪራይ ከፍተኛ ገቢን ታገኛለች።
የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት የሆነችው ጂቡቲ ቁልፍ በሚባለው የቀይ ባሕር ስልታዊው ስፍራ ላይ የምትገኝ ሲሆን በርካታ የዓለማችን ወታደራዊ ኃያል አገራት በአገሪቱ ውስጥ ወታደራዊ ሰፈር አላቸው።












