ለ'ሆቴል ሩዋንዳ' ፊልም መነሻ የሆነው ግለሰብ በሽብር ክስ ጥፋተኛ ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
'ሆቴል ሩዋንዳ' በተባለው ዝነኛ ፊልም ላይ የሕይወት ታሪኩ ታይቶ እውቅናን ያተረፈው ፖል ሩሴሳቢጊና ከሽብር ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ጥፋተኛ ተባለ።
በሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ላይ በሚያጠነጥነው 'ሆቴል ሩዋንዳ' ፊልም ላይ የጀግና ሚና ተላብሶ ታሪኩ የተነገረለት ፖል ካለፈው የካቲት ጀምሮ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ ነበር።
የሩዋንዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ ሰኞ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት፤ ፖል ናሽናል ሊብሬሽን ፍሮንት (ኤፍኤልኤን) የተባለ ሕገወጥ የታጣቂ ቡድን ካቋቋሙ አንዱ በመሆኑ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል። ይህንን ቡድን በገንዘብ ይደግፍ እንደነበርም ፍርድ ቤቱ አመልክቷል።
ግለሰቡ ያለፈው መጋቢት ላይ በሩዋንዳ ፍርድ ቤት ፍትሕ አላገኝም የሚል ምክንያት በማቅረብ ኪጋሊ በሚገኘው ፍርድ ቤት መቅረብ አቁሟል።
ፍርድ ቤቱ እንዳለው፤ ኤፍኤልኤን የተባለው ቡድን እአአ ከ2018 እስከ 2019 በደቡብ ምዕራብ ሩዋንዳ ጥቃቶች ፈጽሟል። በጥቃቶቹ ዘጠኝ ሰዎች ሲሞቱ፣ የተጎዱ ሰዎችን የወደመ ንብረት መኖሩም ተገልጿል።
ፖል በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ ዐቃቤ ሕግ ጠይቋል።
እአአ በ1994 ሩዋንዳ ውስጥ የዘር ጭፍጨፋ ሲፈጸም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በማዳን ስመ ጥር የሆነው ፖል፤ በወቅቱ የአንድ ሆቴል ኃላፊ ነበር።
ፖል ላይ ክስ የተመሠረተው የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜን መተቸት ከጀመረ ወዲህ ነው።
አምና ወደ ብሩንዲ እየተጓዘ የነበረ አውሮፕላን በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ በድንገት ካረፈ በኋላ ነበር በቁጥጥር ሥር የዋለው።
ልጁ ካሪን ካሪምባ፤ "ፍርዱ ፍትሐዊ ይሆናል ብለን አንጠብቅም" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
"አባታችን ጥፋተኛ እንደሚባል እናውቃለን። በሩዋንዳ የፍትሕ ሥርዓት ተስፋ ቆርጠናል። የእኛ ተስፋ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና ዓለም አቀፍ የፍትሕ ሂደት ነው" ብላለች።
የአባቷ አያያዝ ኢፍትሐዊ እንደሆና የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደደረሰበትም ተናግራለች።
የሩዋንዳ መንግሥት በበኩሉ የፖል የፍርድ ሂደት ፍትሐዊ ነው ሲል ይከራከራል።
1994 ላይ ሩዋንዳ ውስጥ በ100 ቀናት ውስጥ 800,000 ሰዎች ተገድለዋል። አብዛኞቹ የቱትሲ ጎሳ ተወላጆች ነበሩ።
ለኦስካር በታጨው 'ሆቴል ሩዋንዳ' ፊልም ላይ ፖልን ወክሎ የሚተውነው ዶን ቼዳሌ ነው። የሆቴል ኃላፊው ከ1,000 በላይ ሰዎችን ከሞትን ሲታደግ ያሳያል።
ፊልሙ 2005 ላይ ለዕይታ ከበቃ በኋላ ፖል ዝነኛ ቢሆንም፤ የካጋሜን አስተዳደር ሲተች የበለጠ እውቅና ማትረፍ ጀምሯል።
በስደት እየኖረ ሳለ ተቃዋሚ ፓርቲ የሆነውን ኤፍኤልኤን መርቷል። ይህ ቡድን የታጣቂ ኃይል ክንፍ ያለው ሲሆን፤ ጥቃቶች በመፈጸም ይወነጀላል።
የፖል ቤተሰቦች እንደሚሉት ፖል አምና ወደ ሩዋንዳ የተወሰደው ታግቶ ነው።
በፍርድ ሂደቱ ላይ ንግግር ያደረጉ አንድ የዓይን እማኝ በበኩላቸው፤ ዱባይ ሳሉ ወደ ሩዋንዳ የሚሄድ አውሮፕላን ላይ ፖል እንዲሳፈር ለማታለል በሚል አውሮፕላኑ ወደ ብሩንዲ እንደሚጓዝ ነግረውታል።












