ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኤል ሳልቫዶር ቢትኮይንን ሕጋዊ መገበያያ በማድረግ የመጀመሪያዋ አገር ሆነች
የማዕካለዊ አሜሪካ አገር ኤል ሳልቫዶር ቢትኮይንን ሕጋዊ መገበያያ በማድረግ የመጀመሪያዋ አገር ሆነች።
ይህ የኤል ሳልቫዶር ውሳኔ በአገሬው ዜጎችና በተቀረው ዓለም ዙሪያ በጥቅሙ እና ጉዳቱ ዙሪያ ሃሳብ እንዲንሸራሸር አድርጓል።
በኤል ሳልቫዶር ከትናንት ጀምሮ ምርት እና አገልግሎት አቅራቢያው ለአገልግሎቱ ክፍያውን በቢትኮይን የመቀበል ግዴታ ተጥሎበታል። ተጠቃሚውም ላገኘው አገልግሎት ክፍያውን በዲጂታል ገንዘብ መክፈል ይችላል።
በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎችም መንግሥት ለግብይት ብሎ ያዘጋጀውን መተግበሪያ ስልካቸው ላይ የሚጭኑ ሲሆን ሰዎችን ለማበረታታትም መንግሥት ለእያንዳንዱ ኤል ሳልቫዶራዊ 30 ዶላር የሚያወጣ ቢትኮይን ይሰጣል።
ይህንን ተከትሎም በመላው ዓለም የሚገኙ የቢትኮይን ደጋፊዎች የኤል ሳልቫዶር መንግሥት ውሳኔን ለመደገፍ 30 ዶላር የሚያወጣ ቢትኮይን በመግዛት ላይ ናቸው።
ባሳለፍነው ሰኔ የኤል ሳልቫዶር ፕሬዝደንት ናይብ ቡኬሌ ቢትኮይን የተባለው ክሪፕቶ ከረንሲ ሕጋዊ እንዲሆን እንደሚያደርጉ ተናግረው ነበር።
ይህ የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ በኮንግረሱ መጽደቁን ተከትሎ ማዕከላዊ አሜሪካዊቷ አገር ኤል ሳልቫዶር ዲጂታል መገበያያን ሕጋዊ በማድረግ የመጀመሪያ አገር ሆናለች።
ቢትኮይን ከአሜሪካ ዶላርና ከኤል ሳልቫዶር ኦፊሴላዊ ገንዘብ እኩል መገበያያ ይሆናል ማለት ነው።
በወቅቱ "ቢትኮይንን ሕጋዊ ማድረግ ሥራ ይፈጥራል፤ እንዲሁም በሺዎች ለሚቆጠሩ በኢ-መደበኛ ሥራ ለተሰማሩ አማራጭ ይሆናል" ሲሉ ፕሬዝደንቱ ፍሎሪዳ በነበረው የቢትኮይን ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
የ26 ዓመቱ ኤል ሳልቫዶራዊ ዳኒኤል ሄርኩለስ የታክሲ አሽከርካሪ ሲሆን በመንግሥት ውሳኔ በጣም እንደተደሰተ ቢገልጽም ምናልባት ገቢው ላይ ጫና እንዳያሳድርበት ግን ስጋት አለው።
"ይህ ውሳኔ እንደሚተላለፍ ካወኩኝ በኋላ ላለፉት ሁለት ወራት ክፍያ በቢትኮይን በኩል ስቀበል ነበር። አንድ ደንበኛ ወደ አየር ማረፊያ ወስጄው 40 ዶላር የሚያወጣ ቢትኮይን ከፈለኝ። 10 በመቶ የሚሆኑት ደንበኞች ብቻ ናቸው በቢትኮይን የሚከፍሉት'' ይላል።
ዳኒኤል እንደሚለው ቢትኮይንን ወደ አገሬው መገበያያ ገንዘብ መቀየር ኪሳራ ያለው ሲሆን በዶላር ደግሞ እስከ 10 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ አለው።
በቅርቡም በስልኩ በሚገኘው መተግበሪያ በኩል እስከ 1 ሺህ ዶላር ድረስ የሚያወጣ ቢትኮይን ለመግዛት ቢያቅድም ምናልባት ሥርአቱ ያልታሰበ ፈተና ቢያጋጥመውስ የሚለው ግን ስጋት ሆኖበታል።
"ከሁሉም በላይ የሚያስጨንቀኝ ቀኑን ሙሉ ሥራ ሥሰራ ውዬ ከስሬ ወደ ቤቴ መግባት ነው'' ብሏል።
ባለፈው ዓመት ብቻ የቢትኮይን ዋጋ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍ እና ዝቅ ሲል ነበር።
ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ የአንድ ቢትኮይን ዋጋ 10 ሺህ ዶላር ከነበረበት ሚያዝያ ወር ላይ በአንድ ጊዜ ወደ 63 ሺህ ዶላር ከፍ ብሏል። በዚህ ዓመት ሰኔ ወር ላይ ደግሞ የአንድ ቢትኮይን ዋጋ ወደ 30 ሺህ ዶላር ዝቅ ብሎ ነበር።
የኤል ሳልቫዶርን ውሳኔ ተከትሎ ደግሞ የአንድ ቢትኮይን ዋጋ ተመልሶ ወደ 51 ሺህ ዶላር ከፍ ማለቱን የዘርፉ ባለሙያዎች አስታውቀዋል።
ነገር ግን የማዕከላዊ አሜሪካ ዩኒቨርሲቲ በሠራው አንድ ጥናት መሠረት በጥናቱ ከተሳተፉት 1281 ሰዎች መካከል 4.8 በመቶ የሚሆኑት ቢትኮይን ምን እንደሆነና እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል አያውቁም።
በጥናቱ ከተሳተፉት ሰዎች መካከል 68 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከነጭራሹ ቢትኮይን ጥቅም ላይ መዋል የለበትም ባይ ናቸው ብሏል ዩኒቨርሲቲው።
ከሁለት ሚሊዮን በላይ ኤል ሳልቫዶራዊያን ከአገራቸው ውጭ ይኖራሉ። በዓመት እስከ 4 ቢሊዮን ዶላር ድረስ ወደ አገር ቤት ይልካሉ። ሰዎች ገንዘብ ወደ ቤታቸው ሲልኩ የመላላኪያ ገንዘብ ይከፍላሉ፤ ተቀባዩ ጋር እስኪደርስም ቀናት ሊወስድበት ይችላል።
ይህ ቢትኮይንን የመጠቀም ውሳኔ የሚሊዮኖችን ሕይወትን እንደሚያሻሽል የመንግሥት እምነት ነው።
በኤል ሳልቫዶር ዶላሮችን ወደ ቢትኮይን መቀየር የሚያስችሉ ከ200 በላይ አዳዲስ ማሽኖች እየተገጠሙ ነው። ነገር ግን በዚህ ውሳኔ ብዙም ምቾት ያልተሰማቸው ዜጎች ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው።
በቅርቡም በዋና ከተማዋ ሳን ሳልቫዶር ዜጎች የመንግሥትን አከራካሪ ውሳኔ በመቃወም ሰልፍ ወጥተው ነበር።
እንደ ቻይና ያሉ በርካታ አገራት ከኤል ሳልቫዶር በተቃራኒው ዲጂታል ግብይትን ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ።
ነገር ግን የዘርፉ ባለሙያዎች ሌሎች አገራትም በቅርብ ዓመታት የኤል ሳልቫዶርን ፈለግ እንደሚከተሉ ይገልጻሉ።