በፈረንሳይ ሊግ የውሃ ኮዳ ተጫዋች ላይ በመወርወሩ ጨዋታው ተቋረጠ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፈረንሳይ ሊግ የውሃ ኮዳ ተጫዋች ላይ በመወርወሩ ኒስ እና ማርሴ ሲያደርጉት የነበረው ጨዋታ እንዲቋረጥ ሆነ።
የማርሴ ተጫዋች ዲሚቲሪ ፓዬ በውሃ ኮዳ ተመትቶ ኮዳውን ወደ ደጋፊዎች መልሶ መወርወሩን ተከትሎ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ በመግባታቸው ጨዋታ እንዲቋረጥ ተደርጓል።
የማርሴው ፓዬ የማዕዘን ምት ሊመታ ሲሰሰናዳ በባለሜዳዎቹ ኒስ ደጋፊዎች በውሃ ኮዳ ጀርባውን ተመቷል።
ተጫዋቹ ኮዳውን መልሶ መወርወሩን ተከትሎ ወደ ሜዳ የገቡ ደጋፊዎችን ጠባቂዎች እና ተጫዋቾች ሊያስቆሟቸው አልቻሉም።
ከረዥም ቆይታ በኋላ የኒስ ተጫዋቾች ጨዋታውን ለመጨረስ ወደ ሜዳ ቢገቡም የማርሴይ ተጫዋቾች ግን ፍቃደኛ አልሆኑም።
በዚህ ምክንያት ጨዋታው ተቋርጧል። በካሴፐር ዶልበርግ የመጀመሪያ አጋማሽ ግብ ባለ ሜዳው ኒስ 1-0 እየመራ ነበር።
አንዳንድ የማርሴይ ተጫዋቾች በተፈጠረው ግርግር ምክንያት ጉዳት እንደደረሰባቸው ተነግሯል።
የማርሴይ ፕሬዝዳንት ፓብሎ ሎኖሪያ "የእኛ ተጫዋቾች ጥቃት ደርሶባቸዋል" ብለዋል።
"በሜዳ ወረራው ወቅት ጥቃት ለደረሰባቸው ተጫዋቾቻችን እና ለሌሎቹም ደህንነት ዋስትና ስላልነበረ ጨዋታው እንዳይቀጥል ወስነናል" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትርምሱ ተጫዋቾች ከሜዳ ለመውጣት ሲሞክሩ ቀጥሏል። የማርሴይ አሰልጣኝ ጆርጅ ሳምፓሊ በሥራ ባልደረቦቻቸው ሲገላገሉ ታይተዋል።
ጨዋታው እየተካሄደም የማርሴይ ተጫዋቾች በማዕዘን ምቱ መምቻ አካባቢ የውሃ ኮዳ ሲወረወርባቸው የነበረ ሲሆን አንዱ ፓዬን በመታቱ አማካዩ ወድቋል።
ይህን ተከትሎ በተፈጠረው አለመግባባት የቡድን ባልደረቦቹ አልቫሮ ጎንዛሌዝ እና ማቲዮ ጉንዶዚ ደጋፊዎቹን ለመጋፈጥ ሲሮጡ የኒሱ ግብ ጠባቂ ዳንቴ ደግሞ ደጋፊዎቹን ለማረጋጋት ሲሞክር ታይቷል።
ማርሴይ ከሁለት ሳምንት በፊት ሞንትፔሊየን 3-2 ባሸነፈችበት ጨዋታም ደጋፊዎች ወደ ሜዳው የውሃ ኮዳዎችን በተመሳሳይ ሲወረውሩ ታይተዋል።
በስታዲየሙ ድምጽ ማጉያ ደጋፊዎች እንዲረጋጉ የጠየቁት የኒሱ ፕሬዝዳንት ዣን ፒዬር ሪቭሬ ለአንዳንድ ጥፋቶች ማርሴዮችን ተጠያቂ አድርገዋል።
"ጨዋታው በዚህ መልኩ መጠናቀቁ ያሳዝናል" ብለዋል።
"ሁሉም የተከሰተውን አይቷል። የውሃ ኮዳዎች እንደተወረወሩ መካድ አንችልም። ግጭቱን ያቀጣጠለው የበቀል እርምጃ በወሰዱት ሁለት የማርሴይ ተጫዋቾች ምላሽ ነበር።
ከዚያ በኋላ የማርሴይ የደህንነት ሠራተኞች ጣልቃ ገብተው ተጫዋቾቻችንን መምታታቸው በጣም የሚያሳዝን ነው።" ሲሉ ተናግረዋል።












