በቤላሩሷ አትሌት ምክንያት የዓለም ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሁለት አሰልጣኞችን አባረረ

ክርስቲሲና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የቤላሩሷ አትሌት ክሪስቲሲና ትሲማኑስካያ ከቶኪዮ ኦሎምፒክ እንድትወጣ ለማስገደድ ሞክረዋል በሚል የሁለት አሰልጣኞችን የኦሊምፒክ ዕውቅና አንስቷል።

አርቱር ሺማክ እና ዩሪ ማይሴቪች የተባሉ አሰልጣኞች ከኦሎምፒክ መንደር እንደወጡ ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) አረጋግጧል። ምርመራውም እንደቀጠለ ነው።

ከቡድን አጋሮቼ ተለይቼ ወደ አገር ቤት ለመመለስ ፈቃደኛ አይደለሁም ያለችው የክሪስቲሲና ትሲማኑስካያ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ትኩረትን ስቧል።

አትሌቷ አሁን ባገኘችው ሰብዓዊ ቪዛ ፖላንድ ትገኛለች።

በስሜታዊነቷ ምክንያት ከብሔራዊ ቡድኑ እንደተወገደች ቤላሩስ አስታውቃ ነበር። ይህ እውነት አይደለም ያለችው የ24 ዓመቷ ሯጭ ስለ 'አሠልጣኞቼ ቸልተኝነት' በኢንስታግራም ላይ ስለተናገርኩ ተባርሬያለሁ ብላለች።

አይኦኦሲ በመግለጫው የሁለቱን አሰልጣኞች ዕውቅና በቶኪዮ ለሚገኙ የቤላሩስ አትሌቶች ደኅንነት ሲባል እንደ ጊዜያዊ እርምጃ አንስቻለሁ ብሏል።

ድርጊቱን የሚያጣራ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ተቋቁሞ ሁለቱም አሰልጣኞች "እንዲደመጡ ዕድል ይሰጣቸዋል" ብሏል።

ትሲማኑስካያ የታገደችው ወደ 4x400 ሜትር ዱላ ቅብብል ውድድር በአጭር ጊዜ ውስጥ መግባቷን በማኅበራዊ ድር አምባ ላይ ቅሬታ ካሰማች በኋላ ነው።

ቪዲዮው በመንግሥት ሚዲያዎች ላይ ትችት ያስከተለባት ሲሆን አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ደግሞ የቡድን መንፈስ እንደሌላት አስከመግለጽ ደርሷል።

ሁለት አሰልጣኞች ወደ ክፍሏ ሄደው ወደ ቤቷ ለመመለስ ቦርሳዎቿን እንድታዘጋጅና ጉዳት እንደደረሰባት እንድትገልጽ ነግረዋት ነበር።

ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ ባለፈው ሳምንት ወደ አውሮፕላን ማረፊያው እየሄደች ሳለ አያቷ ስለ ሁኔታው የዜና ዘገባዎችን ከተመለከቱ በኋላ መመለሷ ጥሩ እንዳልሆነ እንዳስጠነቀቋት ተናግራለች።

አትሌቷ በኃይል ወደ አገሯ እንድትመለስ ጫና በመደረጉ የፖሊስ ጥበቃ አስፈልጓት ነበር። ከዚያም ቶኪዮ በሚገኘው የፖላንድ ኤምባሲ ቆይታ አድርጋ ረቡዕ ወደ ፖላንድ ተጓዘች።

ትሲማኑስካያ "የፖለቲካ ሰው አይደለሁም" ያለች ሲሆን በአትሌቲክስ ሙያዋ ላይ ብቻ ማተኮርም ትፈልጋለች።

"እኔ ስለ ፖለቲካ ምንም አላውቅም። በፖለቲካ ውስጥም በጭራሽ አልነበርኩም" ብላለች።

ሯጯ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ወደ ቤላሩስ መመለስ ብትፈልግም በአሁኑ ጊዜ በጣም አደገኛ ነው።

ባለቤቷም ከቤላሩስ ሸሽቶ የፖላንድ ቪዛ ተሰጥቶታል። ዘመዶቿ ግን አሁንም ቤላሩስ ናቸው።