ወደ አገሬ አልመለስም ያለቸው የቤላሩስ አትሌት ወደ ቪዬና አቀናች

የቤላሩስ አትሌት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ወደ አገሯ እንድትመለስ የተሰጣትን ትዕዛዝ አልቀበልም ያላችው የቤላሩስ አትሌት ከቶኪዮ ወደ ኦስትሪያ፣ ቪዬና አቀናች።

የ24 ዓመቷ ክሪስቲሲና ትሲማኑስካያ ረቡዕ ጠዋት ወደ ፖላንድ ትሄዳለች ተብሎ የነበረ ቢሆንም ቪየና በሚያቀና አውሮፕላን ተሳፍራለች ተብሏል።

ፖላንድ ቪዛ ስለሰጠቻት በቀጥታ ወደ ፖላንድ መዲና ዋርሶ ትጓዛለች ተብሎ ቢጠበቅም በመጨረሻው ሰዓት መዳረሻዋ ተቀይሯል ሲሉ አንድ የአየር ማረፊያው ባለሥልጣን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

አትሌቷ ወደ አገሬ አልመለስም ያለቸው በፖለቲካዊ ምክንያት እንዳልሆነ ለቢቢሲ ተናገረች። "አገሬን እወዳለሁ፤ አገሬን አልከዳሁም" ብላለች።

አትሌቷ ለውሳኔዋ ምክንያቱ "በኦሎምፒክ ባለሥልጣኖቻችን የተፈጠሩ ስህተቶች ናቸው" ብላለች።

አትሌቷ ባለፈው ሳምንት አሰልጣኞቿን በመተቸቷ ዕቃዎቿን ጠቅልላ ወደ ቶኪዮ ሃኔዳ አውሮፕላን ማረፊያ ብትወሰድም ለደኅንነቴ እሰጋለሁ በሚል ወደ ቤላሩስ አልጓዝም ብላ ነበር።

በቶኪዮ ወደሚገኘው የፖላንድ ኤምባሲ ከመዛወሯ በፊት የፖሊስ ጥበቃ የተደረገላት ሲሆን ረቡዕ ወደ አውሮፕላን ማረፊያ እስክትጓዝ ድረስ በኤምባሲው ቆይታለች።

የቤላሩስ አትሌቲክስ ቡድን አትሌቷ ከአዕምሮ ዝግጁነት ጋር በተያያዘ ከብሔራዊ ቡድኑ እንደተቀነሰች አስታውቋል።

ማክሰኞ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረገችው ክሪስቲሲና ትሲማኑስካያ ግን ምንም ዓይነት የአዕምሮ ጤና ችግር እንዳልነበራት እና በኦሎምፒክ መንደሩ ከሐኪሞች ጋር ምንም ውይይት እንዳላደረገች ተናግራለች።

አትሌቷ በአየር ማረፊያ የፖሊስ ጥበቃን ጠይቃ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, አትሌቷ በአየር ማረፊያ የፖሊስ ጥበቃን ጠይቃ ነበር

"የፖለቲካ ነገር ስላልተናገረች" ከውድድሩ እንደምትወጣ ሲነግሯት በጣም እንደተገረመች ተናግራለች።

ደኅንነቷ የተጠበቀ መሆኑን ስታውቅ ወደ ቤላሩስ መመለስ እንደምትፈልግ ገልጻለች። ምናልባት ከአምስት ወይም ከ10 ዓመታት በኋላ መመለስ ይቻላል ብላለች።

ቤላሩስ ክሪስቲሲና ትሲማኑስካያን ወደ አገሯ እንድትመለስ ለማስገደድ ሞክራለች በሚለው ክስ ላይ የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) ምርመራ ጀመሯል።

የአይኦሲው ቃል አቀባይ ማርክ አዳምስ "ሙሉ እውነታውን ማግኘት አለብን። ያ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። እስከዚያ ድረስ የእኛ የመጀመሪያ ጉዳይ አትሌቷ ናት" ብለዋል።

የቤላሩስ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሪፖርቱን እስከ ማክሰኞ ድረስ እንዲያቀርብ አይኦሲ ጠይቋል።