ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ በአሜሪካ ሳን ዲዬጎ የኮቪድ-19 የሙከራ ክትባት ለጎሬላዎች ተሰጠ
በአሜሪካው የሳን ዲዬጎ እንስሳት ማቆያ የሚገኙ ጎሪላዎች በኮሮናቫይረስ መጠቃታቸውን ተከትሎ ለእንስሳት ተብሎ የተሠራ የሙከራ የኮቪድ-19 ክትባት ለእንስሳቱ ተሰጠ።
በእንስሳት መድኃኒት አምራች ድርጅቱ ዞይቲስ የተሠራ ክትባት ለዘጠኝ ዝንጀሮዎች ሁለት ጊዜ እንዲሰጣቸው ተደርጓል።
በእንስሳት ማቆያ ውስጥ የሚገኙ ስምንት ጎሪላዎች በጥር ወር ኮቪድ-19 የተገኘባቸው ሲሆን አሁን እያገገሙ ነው።
የእንስሳት ጥበቃ ባለሙያዎች ኮቪድ-19 በእንስሳቱ መከሰቱ ስጋት ፈጥሮባቸዋል።በተለይም በመጥፋት አደጋ ዝርዝር ውስጥ የገቡት ጎሪላዎች ጉዳይ ይበልጥ አሳስቧቸዋል ተብሏል።
ከአያ አምስት ዓመታት በፊት የልብ ቀዶ ህክምና በማግኘት በዓለም የመጀመሪያዋ ኦራንጉተን [የጎሬላ ዝርያ] የሆነችው 'ካረን' ክትባቱ ከተሰጣቸው መካከል አንዷ ነች።
በሳን ዲዬጎ የእነስሳት ማቆያ ዋና ኃላፊ ናዲን ላምበርስኪ ዝንጀሮዎቹ ክትባቱን ካገኙ በኋላ ምንም ዓይነት አሉታዊ ውጤት እንዳላሳዩና የክትባቱን ስኬታማነት ለማወቅ ለመለየት በቅርቡ ምርምራ ይደረግባቸዋል ብለዋል።
በኒው ዮርክ ብሮንክስ፣ በስፔን ባርሴሎና እና በሌሎችም የእንስሳት ማቆያዎች አንበሶችን እና ነብሮችን ጨምሮ ሌሎች እንስሳት በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል።
የኮሮናቫይረስ ከሰው ባሻገር ውሾችና ድመቶችን ጨምሮ በሌሎችም እንስሳት ላይ መኖሩ ተረጋግጧል። ቢሆንም ግን የበሽታው ስርጭት በጣም ዝቅተኛ ነው።
መድኃኒት አምራቹ ዞይቲስ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር አንድ ውሻ ሆንግ ኮንግ ውስጥ በቫይረሱ መያዙ ከተረጋገጠ በኋላ ነበረት ለድመቶችና ለውሾች የኮቪድ-19 ክትባት ማዘጋጀት የጀመረው።
ክትባቱ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ድመቶችና ውሾች ላይ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ውጤታማ እንደሆነ ተረጋግጧል፤ እስከ የካቲት ድረስም ክትባቱ በሌሎች እንስሳት ላይ አልተሞከረም።
ላምበርስኪ ለናሽናል ጂኦግራፊክ እንደተናገሩት ዝንጀሮዎቹን መከተብ ከሚያስከተለው ችግር ይልቅ የሚኖረው ጠቀሜታ ይልቃል።
ጨምረውም "በተለምዶ ለውሾችና ለድመቶች የታቀዱ ክትባቶችን ለአንበሶችና ለነብሮች እንጠቀማለን" ብለዋል።