ምርጫ 2013፡ምርጫ ቦርድ በድምጽ መስጫ ዕለት አስጊ የጸጥታ ሁኔታ የለም አለ

የድምፅ መስጫ ወረቀት ማሳያ

የፎቶው ባለመብት, National Electoral Board of Ethiopia- NEBE

ታትሟል

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በድምጽ መስጫ ዕለት መሠረታዊ የሆነ የጸጥታ ስጋት አያጋጥመኝም አለ።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፊታችን ሰኞ ሰኔ 14፣ 2013 ዓ.ም በሚደረገው 6ኛው አገራዊ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን ላይ መሠረታዊ የሆነ የጸጥታ ችግር ይገጥማል ተብሎ አይጠበቅም ብሏል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሚኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ፤ የጸጥታ ችግር ያለባቸው አከባቢዎች ተለይተው በልዩ ሁኔታ ምርጫ የሚሰጡበት ወቅት ወደ ጵጉሜ 1 2013 ዓ.ም. መሸጋገሩን አስታውሰው የፊታችን ሰኞ በሚካሄደው የድምጽ አሰጣጥ ላይ መሠረታዊ የሆኑ የጸጥታ ችግር ያጋጥማል ተብሎ አይታሰብም ብለዋል።

በድምጽ መስጫ ቀን የተከለከሉ ተግባራት

ሶሊያና ሽመልስ በዛሬው ዕለት ሰኔ 11፣ 2013 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ በድምጽ መስጫ ቀናት የተከለከሉ ተግባራትን ዘርዝረዋል።

ድምጽ በሚሰጥበት ምርጫ ጣቢያ ድምጽ ለመስጠት ካልሆነ በቀር ፍቃድ የሌለው ማንኛውም ሰው በምርጫ ጣቢያው 200 ሜትር ክልል ውስጥ መግባት አይችልም ብለዋል።

ከምርጫ አስፈፃሚዎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና የግል እጩ ወኪሎች እና ከተፈቀደላቸው የምርጫ ታዛቢዎች በስተቀር መራጮች ያልሆኑና ድምፅ የሰጡ ሰዎች በምርጫ ጣቢያው ክልል ውስጥ መገኘት የለባቸውም ተብሏል።

ድምጽ ለመስጥት የሚገባን እና ድምጽ ሰጥቶ የሚወጣን ሰው ቆሞ መመልከት፣ ምልክት ማሳየት፣ ማስፈራራት፣ ማባበል እና የመሳሰሉት ተግባራትን መፈጸም የተከለከሉ መሆኑን ሶሊያና አስረድተዋል።

የፓርቲዎችን አርማ የያዙ ቲሸርቶችን አልባሳትን፣ ፖስተሮችን ይዞ ወይም የሚደግፉትን ፓርቲ ምልክት ይዞ ወደ ምርጫ ጣቢያ መሄድ አይቻልም።

የጦር መሳሪያ ይዞ ወደ ምርጫ ጣቢያ መሄድ የተከለከለ መሆኑንም ሶሊያና አስረድተዋል።

የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቢሆኑ በምርጫ ጣቢያ 200 ሜትር ክልል ውስጥ መግባት አይችሉም ብለዋል።

ጸጥታ አስከባሪዎች ከምርጫው አስፈጻሚ ጥያቄ ከቀረበላቸው ብቻ ወደ ምርጫ ጣቢያ ሊገቡ እንደሚችሉ አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በምርጫ ዕለት ምንም አይነት የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄድ አይቻልም ብለዋል። "ወጥታችሁ ምረጡ የሚል ቅስቀሳንም ማድረግ ፈጽሞ የተከለከለ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ፍቃድ ያላቸውን የፓርቲ ወኪሎችን እና የጋዜጠኞች እንቅስቃሴ ማስተጓጎል እንደማይቻልም አስረድተዋል ሶሊያና።

"ምርጫ ጣቢያ ውስጥ መግባት አትችሉም፣ ወደዚህ መሄድ አትችሉም በማለት ክልከላ ማድረግ የተከለከለ ነው" ብለዋል።

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ የመራጮች ቁጥር 38 ሚሊዮን 234 ሺህ 910 መሆኑን ተናግረዋል ምርጫውን ለመታዘብ እየገቡ ያሉ የውጪ አገር ታዛቢዎች መኖራቸውን አስታውሰዋል።

መስመር