ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የካሊፎርኒያ ፍርድ ቤት ከክሊኒክ የዘር እንቁላልና ጽንስ ለጠፋባቸው 15 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ወሰነ
አንድ የካሊፎርኒያ ፍርድ ቤት በአውሮፓውያኑ 2018 ክሊኒክ በሚገኝ ማቀዝቀዣ ውስጥ የተቀመጠ የዘር እንቁላል ወይም ጽንስ ለጠፋባቸው አምስት ታካሚዎች 14.9 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈል ወሰነ።
በሳንፍራንሲስኮ የሚገኘው ፓስፊክ ፈርቲሊቲ ማዕከል ውስጥ ያለው የክሪዮጂን ማከማቻ (በአነስተኛ የሙቀት መጠን ዕቃ የሚቀመጥበት በርሜል) መበላሸቱን ተከትሎ 3,500 የዘር እንቁላል፣ ጽንስ እና ሌሎችም የዘረ መል አይነቶች ጠፍተዋል።
የሕግ ባለሙያዎቹ የማከማቻውን ብልሽት ተጠያቂ አድርገዋል። በክሊኒክ የማቀዝቀዣ ችግር ለተጎዱ ሰዎች ካሳ ሲከፈል ይህ የመጀመሪያው ነው ይላሉ ጠበቆች።
ሦስት ሴቶች እና ባልና ሚስት የቀዘቀዙ እንቁላሎቻቸውን እና ጽንሶቻቸውን በማጣታቸውን 15 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋውን ካሳይጋራሉ።
ማከማቻ አምራቹ ቻርት ኢንዱስትሪ ኢንክ 90 በመቶውን ካሳ ሲከፍል ክሊኒኩ ለቀሪው 10 በመቶ ተጠያቂ ነው።
በቻርት የተሠራው ማከማቻ ለአጭር ጊዜ ፈሳሽ ናይትሮጂን በማጣቱ አንዳንድ የቀዘቀዙ ነገሮች እንዲጠፉ ምክንያት ሆኗል ብሏል ማዕከሉ።
የቻርት ኢንዱስትሪዎች በማከማቻው ውስጥ ጉድለት እንዳለ ቢያውቅም ምርቱን አልመለሰም መባሉን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የፓስፊክ ፈርቲሊቲ እና የቻርት ኢንዱስትሪዎች ለቢቢሲ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።
ዳኞች፤ ማዕከሉም ሆነ ማቀዝቀዣ ሠሪው ቸልተኛ ሆነው ብዙዎችን እንዳሳዘኑ ተገንዝበዋል ብለዋል።
በችግሩ ምክንያት የዘር ፍሬ ያጣችው የ39 ዓመቷ ክሎዊ ፖይተን ልጅ የመውለድ ዕድሏ እንደጠበበ አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘግቧል።
"በእውነቱ ልጅ እንደማያገኙ እያወቁ በሰው 'ቤቢ ሻወር' ላይ መገኘት በጣም ያሳምማል" ስትል ፍርድ ቤት ቀርባ ተናግራለች።
አምስቱን ከሳሾች ከወከሉ ጠበቆች መካከል አንዷ የሆነኑት ዲና ሻርፕ፤ ፍርዱን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ "ዛሬ በችሎት አዳራሽ ውስጥ የነበረው ስሜት የሚገርም ነበር" ብለዋል።
"ለዓመታት ከደንበኞቻችን ጋር በመሥራት ላይ ብንሆንም ይህ አሰቃቂ ክስተት በታካሚዎች ሕይወት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ሊቀንስ አይችልም።"
ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ክሶችም በማዕከሉ እና በአምራቹ ላይ ቀርበው በመታየት ላይ ናቸው። ጉዳዮቹ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ይታያሉ ተብሎም ይጠበቃል።
እአአ የካቲት 4/2018 የደረሰውን ብልሽት ተከትሎ ክሊኒኩ በሰጠው መግለጫ "ይህ በመከሰቱ እና በሚያስከትለው ጭንቀት በእውነቱ እናዝናለን" ብሏል።
በተመሳሳይ ቀን በክሌቭላንድ ፈርቲሊቲ ክሊኒክ ሌላ ማከማቻ በመበላሸቱ ምክንያት ከ4,000 በላይ እንቁላሎች እና ጽንሶች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል።