የዓለማችን ውዱ የመኪና ማቆሚያ ቦታ በ1.3 ሚሊየን ዶላር ተሸጠ

ሆንግ ኮንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ሆንግ ኮንግ ውስጥ አንድ የመኪና ማቆሚያ አገልግሎት የሚሰጥ ቦታ በዓለማችን ውድ በሆነ 1.3 ሚሊየን ዶላር ዋጋ መሸጡ ተሰምቷል።

የሆንግ ኮንግ መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት በከተማዋ በጣም ምርጥ በሚባለው መኖሪያ አካባቢ የሚገኘው የመኪና ማቆሚያ እጅግ ቅንጡ ከሚባሉት መካከል ነው።

'ማውንት ኒኮልሰን' የተባለው የግንባታና የቤቶች ሽያጭ ድርጅት እሲያ ውስጥ በጣም ውድ የሆኑ መኖሪያ ቤቶችን የሚያስተዳድር ሲሆን፤ በሆንግ ኮንግም 'ቪችቶሪያ ሃርበር' የተባለውን ውድ አካባቢም ያስተዳድራል።

ይሄው ድርጅት ነው ታዲያ በዓለማችን ውድ የተባለውን የመኪና ማቆሚያ ቦታ የሚያስተዳድረው።

ሆንግ ኮንግ በጣም የተጨናነቀች ከተማ መሆኗን ተከትሎ በ1.3 ሚሊየን ዶላር ዋጋ የተሸጠው ቦታ ለመኖሪያም ሆነ ለመኪና ማቆሚያ አገልግሎት ቢውል የበርካታ ሰዎችን ቀልብ መሳብ እንደሚችል ከወዲሁ ተገምቷል።

በዓለማችን ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር ከሚካሄድባቸው ከተሞች አንዷ የሆነችው ሆንግ ኮንግ በጣም ውድ የሚባሉ መኖሪያ ቤቶች እንደሚገኙባት ይገመታል። ከተማዋ ለኑሮ ምቹ ብትሆንም የኑሮ ዋጋ ግን በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል።

ከዚህ በፊት ለመኪና ማቆሚያ ቦታ ከፍተኛው ዋጋ የተከፈለው በዛው ሆንግ ኮንግ ውስጥ ሲሆን፤ በወቅቱ በአውሮፓውያኑ 2019፤ 980 ሺህ ዶላር ነበር ወጪ የተደረገበት።

ለማውንት ኒኮልሰን የሽያጭ ሥራውን የሚያከናውንለት 'ዊሎክ ፕሮፐርቲስ' በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ከቢቢሲ የተጠየቀ ቢሆንም እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።

በቅርብ ወራት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጫት በመጠኑም ቢሆን መቀነሱን ተከትሎ በሆንግ ኮንግ የንግድ እንቅስቃሴዎች እየደሩ ነው። ገዢዎችም ቢሆኑ በርካታ ሚሊየኖችን እያወጡ ቅንጡ ቤቶችና ሌሎች ቦታዎችን እየገዙ ነው።

ባለፈው ወር በከተማዋ የሚገኝ አንድ ቅንጡ መኖሪያ ቤት የዓለም ሪከርድ በሆነ 210 ሺህ ዶላር በወር ተከራይቷል።