ፈረንሳይ ከማሊ ጋር ያላትን ወታደራዊ ግንኙነት አቋረጠች

ፈረንሳይ ከማሊ ጋር ያላትን ወታደራዊ ግንኘነት አቋረጠች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በማሊ ባለፈው ሳምንት የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ፈረንሳይ ከአገሪቱ ጋር በጥምረት ታካሂዳቸው የነበሩ ወታደራዊ ተልዕኮዎችን አቋረጠች።

በማሊ ወታደራዊ መንግሥቱ ሥልጣኑን ለሲቪል ኃላፊዎች የማያስረክብ ከሆነ ፈረንሳይ በዚህ ውሳኔዋ ጸንታ እንደምትቆይ ተገልጿል።

ፈረንሳይ ወታደሮች በሳህል ክልል የሚገኙ ታጣቂዎችን ለመዋጋት በማሊ፣ ቻድ፣ ሞሪታንያ፣ ኒጀር እና ቡርኪና ፋሶ ወታደሮቿችን አሰማርታ ትገኛለች።

ከዘጠኝ ቀናት በፊት በማሊ ወታደራዊ ሥልጣን ያላቸው ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ የአገሪቱን ፕሬዝዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ከሰልጣን አባረው በቁጥጥር ሥር አውለዋቸው ነበር።

በያዝነው ሳምንት የምሥራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ቡድን ኢኮዋስ እና የአፍሪካ ሕብረት ማሊን ከአባልነት ሰርዘዋታል። ሐሙስ ዕለት ደግሞ ኢኮዋስና የአፍሪካ ሕብረት ያስተላለፉት ውሳኔ በማሊ ሊኖር ስለሚገባው ፖለቲካዊ መረጋጋት መሠረት የሚጥል ነው ብሏል የፈረንሳይ መከላከያ ኃይል።

አክሎም "እነዚህን ማረጋገጫዎች እስከምናገኝ ድረስ ፈረንሳይ ለጊዜው ከማሊ መከላከያ ኃይል ጋር ታካሂዳቸው የነበሩ ጥምር ወታደራዊ ተልዕኮዎችን ለማቋረጥ ወስናለች'' ብሏል።

ነገር ግን የፈረንሳይ ወታደሮች ያለማንም ጣልቃ ገብነት በአካባቢው እንደሚንቀሳቀሱ ተገልጿል።

በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ፤ በማሊ ያለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ወደ ኢስላማዊ አክራሪነት አገሪቱን የሚመራት ከሆነ ፈረንሳይ ወታደሮቿን እንደምታስወጣ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ማስጠንቀቃቸው የሚታወስ ነው።

ፈረንሳይ በምዕራብ አፍሪካ ሳህል አካባቢ 5100 ወታደሮችን ያሰፈረች ሲሆን ለበርካታ ዓመታት ኢስላማዊ ታጣቂዎችን ስትዋጋ ቆይታለች።

ላለፉት አሥርት ዓመታት ፈረንሳይ በቀድሞ የቅኝ ግዛቷ ሥር ለነበሩ አገራት መሪዎች ወታደራዊ ድጋፍ ስታደርግ የቆየች ሲሆን፤ አብዛኛውን ጊዜም ወታደሮችን በመላክና አማጺያን ላይ የአየር ድብደባ በማድረግ ትሳተፋለች።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት በነበሩት ማሊና ቻድ ያለው አለመረጋጋት ፕሬዝደንት ማክሮንን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ማሊ ውስጥ ሁለት መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደ ሲሆን በቻድ ደግሞ አንድ መፈንቅል መንግሥት ተደርጓል።

ፕሬዝዳንቱም በሁለቱ አገራት ያለው ወታደራዊ አገዛዝ እንዲቆም ሲጠይቁ ነበር። ማሊ ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ አገሪቱን ወደ አክራሪ ኢስላማዊ አስተዳደር የሚመራት ከሆነ ወታደሮቻቸውን እንደሚያስወጡም ዝተዋል።

ነገር ግን የፈረንሳይ ጦር ከአከባቢው ጠቅልሎ የሚወጣ ከሆነ አክራሪ ኢስላማዊ ቡድኖች በስፋት መንቀሳቀስ እንዳይጀምሩ ስጋት ፈጥሯል።

በማሊ የተፈጠረው ምንድነው?

ባለፈው ሳምንት የማሊ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት በአገሪቱ የተደረገው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት መሪ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታን የሽግግር ጊዜ ፕሬዝዳንት አድርጎ ሰይሟል።

ኮሎኔል ጎይታ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ሁለተኛውን መፈንቅለ መንግሥት አድርገው ሥልጣን ከያዙ ከሁለት ቀናት በኋላ ባለፈው ረቡዕ የማሊ ጊዜያዊ መንግሥት ፕሬዝደንት አድርገው እራሳቸውን ሾመዋል።

በምርጫ ሥልጣን ይዘው የነበሩትን ፕሬዝዳንት ቡባካር ኬይታን ከመንበራቸው ባለፈው ነሐሴ ያስወገዱት ወታደራዊ መሪው፤ የፕሬዝደንትነት ቦታውን እንዲይዙ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

ከመጀመሪያው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ ማሊን ወደ ሲቪል መንግሥት የሚመልሰውን አስተዳደር በጊዜያዊ ፕሬዝዳንትነት እና በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመሩ የነበሩት ባህ ዳዋ እና ሞክታር ኦኔ በሁለተኛው መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎች ተይዘው ታስረዋል።