የቻምፒዮንስ ሊጉ ዋንጫ ወደ ማንችስተር ሲቲ ወይስ ቼልሲ?

የቻምፒዮንስ ሊጉ ዋንጫ ወደ ማንችስተር ሲቲ ወይስ ቼልሲ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ዛሬ በእንግሊዝ ቡድኖች መካከል የሚደረግ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ነው። የዛሬ ምሽቱን የአውሮፓ ቻምፒዮንነት ዘውድ የሚጭነው ማንችስተር ሲቲ ወይስ ቼልሲ?

የፕሪሚየር ሊጉ ቻምፒዮን ማንችስተር ሲቲ ባለ ትልቁን ጆሮ ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማንሳት ይፎካከራል፡፡

የ2012 የአውሮፓ ቻምፒዮኑ ቼልሲ የፔፕ ጋርዲዮላን ቡድን ዘንድሮ በሊጉ እና በኤፍኤ ካፕ ሁለት ጊዜ ማሸነፍ ችሏል።

በፖርቶ ስታዲዮ ዶ ድራጋዎ የሚደረገውን ጨዋታ ለመመልከት እስከ 16,500 ታዳሚዎች እንዲገቡ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

ምንም እንኳን አርብ በተደረገው ልምምድ ላይ የሲቲው አማካይ ኢካይ ጉንዶጋን ከፈርናንድኒሆ ጋር ተጋጭቶ ትንሽ ጉዳት ያስተናገደ ቢመስልም የሁለቱም ቡድኖች ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ።

አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ "መጫወት የምንፈልገውን መንገድ እና ከማን ጋር እንደምንጫወት ስለምናውቅ ብዙ እንደማላስቸግራቸው አውቃለሁ" ብሏል፡፡

"እዚህ መገኘት አስገራሚ ተሞክሮ ነው፡፡ ምን እንደምነግራቸው በትክክልም አውቃለሁ፡፡ የተጨነቁ እና የተደናገጡ ካሉ የተለመደ ነገር እንደሆነ እነግራቸዋለሁ" ሲል ሐሳቡን ሰጥቷል።

በተጨማሪም "የፍፃሜ ጨዋታውን ለማሸነፍ እንደምንሰቃይ እርግጠኛ ነኝ፡፡ [በጨዋታው] ተዝናኑበት ማለት ጥሩ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ አይቻልም፡፡ ጽናት እና ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልጋል" ብሏል፡፡

የሲቲው አማካይ ኬቪን ደ ብሩይን በበኩሉ "ካሸነፍክ ጀግና ነህ፣ ከተሸነፍክ ደግሞ ወድቀሀል ማለት ነው። ወደዚህ ደረጃ መምጣት ለቡድኑ አስደናቂ ቢሆንም ዋንጫውን አለማሸነፍ ግን ልምድ አይደለም" ሲል ገልጿል፡፡

"ከክለቡ እና ከተጫዋቾች ግቦች አንዱ ነው፡፡ እዚህ መድረስ መቻል እና በዓለም ላይ ከፍተኛ በሆነው መድረክ ላይ መጫወት መቻል ትልቅ ዕድል ነው፡፡"

የሲቲው ስፔናዊ አለቃ ጋርዲዮላ በ2009 እና 2011 ከባርሴሎና ጋር ድሉን ከተቀዳጀ በኋላ ሻምፒዮንስ ሊጉን ለሦስተኛ ጊዜ ለማሸነፍ ይጫወታል፡፡

የቼልሲው አለቃ ቶማስ ቱቼል የመጀመሪያውን የቻምፒየንስ ሊግ ስኬት ለማስመዝገብ ይጫወታል፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን ጀርመናዊው ፓሪስ ሴንት ዠርሜንን ይዞ በባየር ሙኒክ 1-0 ተሸንፎ ዋንጫውን አጥቷል፡፡

"ሁሉም እንደሚፈልገው ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ የድል ረሀብ አለ። እናም ሁልጊዜ በስፖርቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ምን ያህል ፍላጎት አለ የሚለው ነው ዋናው ነገር። በዚህ ሳምንት በጣም የተጠናከርን፣ ትኩረት እና ሥነምግባር ያለን ሆኖ ተሰምቶኛል" ብሏል ቱቼል፡፡

"ፔፕ የያዘውን ሲቲ፣ ባየርን ወይም ባርሴሎናን መግጠም ሁልጊዜም ከባድ ነው፡፡ እሱ ትልቅ እምነት እና ስኬት ከመፍጠር ባለፈ ትልቅ የማሸነፍ አስተሳሰብ አለው" ሲል ገልጿል፡፡

"ምናልባትም በአሁኑ ወቅት በአውሮፓ ብሎም በዓለም በጣም ጠንካራው ቡድን ነው። በሊጉ በመካከላችን ትልቅ ክፍተት ቢኖርም በዌምብሌይ እና በማንችስተር ክፍተቱን ዘግተናል" ብሏል፡፡

የዋንጫው ጨዋታ በ90 ደቂቃ የሚወሰን ሲሆን ካልሆነ 30 ደቂቃዎች ተጨማሪ ጊዜ እና አስፈላጊ ከሆነም ወደ ፍጹም ቅጣት ምት ያመራል፡፡

በመደበኛው ክፍለ ጊዜ ቡድኖቹ አምስት ተጫዋቾችን የሚቀይሩ ሲሆን ወደተጨማሪ ሰዓት ካመሩ ደግሞ ተጨማሪ አንድ ተጫዋች የመምረጥ መብት አላቸው፡፡

ቱቼል "በፍጹም ቅጣት ምት በኩል [የዩሮፓ ሊግ ፍፃሜ] ከመቺዎች ጥራት አንፃር ድንቅ ነበር፡፡ 20 ፍጹም ቅጣት ምት ሳይሳት ሲቆጠር የመሰለን ነገር ያየሁ አይመስለኝም" ብሏል።

"ቅጣት ምቱን የሚመቱትን ለይተናል። ነገር ግን በመጨረሻው ሜዳ ላይ ማን እንደሚቆይ አላውቅም። ስለዚህ በደንብ ማወቅ አለብን። ወደ ቅጣት ምት ከሄድን አብረን እንሄዳለን እና አብረን እንወጣለን፡፡"

የቪድዮ ረዳት ዳኛ (ቫር) ጥቅም ላይ ይውላል። ሲቲ ደግሞ 'በሜዳው የሚጫወተው' ቡድን ተብሎ የተሰየመ ሲሆን፤ በዚህም በተለመደው ሰማያዊ እና ነጭ መለያው ይጫወታል፡፡

የዘንድሮው ፍጻሜ በዓለም ዙሪያ ባሉ ከ200 በላይ አገራት ይተላለፋል። የአውሮፓ ክለቦች ትልቁ ጨዋታ ከመጀመሩ 10 ደቂቃ በፊት የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ይደረጋል፡፡