ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሙሴቬኒ ለ6ኛ ዙር ኡጋንዳን ለመምራት ዛሬ ቃለ መሃላ ይፈጽማሉ
የኡጋንዳው ፕሬዘዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ባለፈው ጥር ወር ላይ የተካሄደውን አወዛጋቢ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ አሸንፊያለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ለስድስተኛ ዙር አገሪቱን ለመምራት ዛሬ ቃለ መሃላ ይፈፅማሉ።
ሙሴቬኒ ናሽናል ሬዚስታንስ ሙቭመንት የተባለው ፓርቲያቸው ለአምስት ዓመት በቆየ ጦርነት ማብቂያ ላይ በጎርጎሮሳዊያኑ 1986 ወደ ስልጣን የመጡ ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ኡጋንዳን እየመሩ ይገኛሉ።
የበአለ ሲመቱን ፀጥታ ለማስጠበቅም በኡጋንዳ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፀጥታ ሃይሎች ታድመዋል፡፡ በአለ ሲመቱን ለመታደምም የሶማሊያ እና የቡሩንዲን ጨምሮ የተለያዩ አገራት መሪዎች በኡጋንዳ ከተመዋል።
በዓለ ሲመቱን ተከትሎ በአገሪቱ ከፍተኛ የሆነ ጥበቃ እየተደረገ ነው። ፖሊስ በከተማው እስካሁን ድረስ ከ40 በላይ ሰዎንች መቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል። እንደሁም ሙሴቬኒን በምርጫው ሲገዳደር የቆየው የሮበርት ካያጉላኒ ወይም ቦቢ ዋይን በሚል ስሙ የሚታወቀው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ቤትም በፀጥታ ሃይሎች ተከቧል።
እንዲሁም ኡጋንዳን ለቆ መውጣቱን ከወር በፊት ያስታወቀው ተቃዋሚ ኪዛ ቤሲጊ መኖሪያ ቤትም በፀጥታ ሃይሎች እየተጠበቀ እንደሆነ ተገልጿል።
ሙሴቬኒ ደጋፊዎቻቸው አንጻራዊ ሰላምን እና እድገት በሀገሪቱ በማምጣት በተለይም በጤና ላይ በተከተሏቸው ፖሊሲዎች ያወድሷቸዋል። የኤች አይቪ ስርጭትን በመግታት እና በቅርቡም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቋቋም ሠርተዋል።
በአንድ ወቅት በምዕራቡ ዓለም ከአዳዲሶቹ የአፍሪካ መሪዎች አንዱ ተብለው ቢወደሱም፣ ተቺዎቻቸው ወደ አምባገነን መሪነት ተለውጠዋል ሲሉ ይከሷቸዋል።
ሙሴቬኒ በፓርቲያቸው ውስጥ ተተኪ የሌላቸው ሲሆን እ.ኤ.አ በ2017 ደግሞ 75 የነበረውን የፕሬዚዳንቱን የዕድሜ ገደብ በማንሳት እንደገና ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር የሚያስችላቸውን ሕግ ፈርመዋል።