መካከለኛው ምስራቅ፡ የአፍጋኒስታን ወላጆች በቦምብ ጥቃት የተገደሉ ልጆቻቸውን ቀበሩ

የአፍጋኒስታን ወላጆች በቦምብ ጥቃት የተገደሉ ልጆቻቸውን ሲቀብሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአፍጋኒስታን ወላጆች በቦምብ ጥቃት የተገደሉ ልጆቻቸውን ሲቀብሩ
ታትሟል

በሳለፍነው ቅዳሜ ቅዳሜ ዕለት በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል ትምህርት ቤት አቅራቢያ በደረሰ ፍንዳታ ምክንያት ህይወታቸው ያለፉ ተማሪዎች ቀብር ተፈጸመ።

ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ሲወጡ በደረሰው ፍንዳታ ከ60 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን አብዛኛዎቹ ደግሞ ሴት ተማሪዎች ናቸው።

በሱኒ ኢስላማዊ ታጣቂዎች በብዛት ጥቃት በሚደርስበት ዳሽት ኢ ባርቺ በሚባለው አካባቢ ለደረስ ይህ ጥቃት እስካሁን ድረስ የትኛውም ቡድን ኃላፊነቱን አልወሰደም።

የአፍጋን መንግሥት ለጥቃቱ ተጠያቁዎች የታሊባን ታጣቂዎች ናቸው ቢልም ቡድኑ ግን ከጥቃቱ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለኝም ብሏል።

በቅዳሜው ጥቃት በትክክል ኢላማ የተደረገው ማን እንደሆነ አልታወቀም። አሜሪካ በመጪው መስከረም ወር ወታደሮቿን ከአፍጋኒስታን ሙሉ በሙሉ ጠቅልላ ለማስወጣት ደፋ ቀና በምትልበት ወቅት ይህ ጥቃት መሰንዘሩ ወደፊት ከዚህም የባሱ ጥቃቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ማሳያ ነው ተብሏል።

ከዚህ ቀደም በታሊባን ተጣቂዎች ጥቃት የተሰነዘረባት እና የኖቤል ሽልማት አሸናፊዋ ማላላ ዩሳፍዛይ በትዊተር ገጿ ላይ ጥቃቱን ''ጭካኔ የተሞላበት'' በማለት ገልጸዋለች።

''ልቤ በካቡል ትምህርት ቤት ከተጎዱትና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ነው'' ስትል ጽፋለች።

ቤተሰቦች በጥቃቱ የተገደሉ የልጆቻቸውን አስክሬን ለመቅበር ወደ መቃብር ስፍራ ይዘው ሲሄዱ የሚያሳዩ ምስሎች በስፋት ተሰራጭቷል።

''የፍንዳታውን ድምጽ ስሰማ ወደቦታው ቶሎ ሄድኩኝ። ስደርስ ግን እራሴን በአስክሬን ተከብቤ አገኘሁት። ሁሉም ሴት ታዳጊዎች ናቸው። አስክሬናቸው አንደኛው በሌላኛው ላይ ተደራርቦ ነበር'' ብሏል አንድ ነዋሪ ለኤኤፍፒ ሲናገር።

አንዲት ከጥቃቱ የተረፈች ታዳጊ ደግሞ ፍንዳታው ሲደርስ ከትምህርት ቤት እየወጣች እንደነበር ገልጻለች።

''የክፍል ጓደኞቼ ሞተዋል። ትንሽ ቆይቶ ሁለተኛ ፍንዳታም ነበር። ቀጥሎም ሌላ ፍንዳታ። ሁሉም ሰው እየጮኀ በደም ተለውሶ እየተሯሯጠ ነበር'' ብላለች።

በጥቃቱ ተጨማሪ ከ150 በላይ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከካቡል እየወጡ ባሉ መረጃዎች መሠረት ከተማዋ የኢድን መቃረብ ተከትሎ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ እያስረተናገደች ነበር።

ታሊባን ትናንት ዕሁድ ባወጣው መግለጫ የቅዱስ ረመዳን ጾም ወር መገባደዱን በማስመልከት መላው ሙስሊሞች በዓሉን ተረጋግተው እንዲያከብሩ ለሶስት ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ሀሳብ አቅርቧል።

የአፍጋን መንግስትም ሀሳቡን ተቀብሎ በአሉ እንደሚከበር ይጠበቃል።