ኮሮናቫይረስ፡ የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን የውጭ አገራት ጎብኚዎችን ለማስገባት እያቀደ ነው

ታትሟል

የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ከሌሎች አገራት የሚመጡ ጎብኚዎችን ለማስተናገድ አዲስ እቅድ እያዘጋጀ እንደሆነ አስታውቋል።

በእቅዱ መሰረት በአውሮፓ ሕብረት ፈቃድ ያገኙ ክትባቶችን ከጉዟቸው ሁለት ሳምንታት በፊት ቢያንስ አንድ ጊዜ የወሰዱ ተጓዦች እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል።

''ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ የአውሮፓ ሕብረትን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃትና የድንበር ተሻጋሪ ወዳጅነትን ለማጠናከር ጊዜው አሁን ነው'' ብለዋል የኮሚሽኑ ፕሬዝደንት አርስላ ቮን በትዊተር ገጻቸው ላይ።

በአሁኑ ሰአት የአውሮፓ ሕብረት በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ጉዞዎች ውጪ ተጓዦችን የሚቀበለው ከሰባት አገራት ብቻ ነው።

ነገር ግን በእቅዱ ውስጥ ለድንገተኛ አጋጣሚዎች የሚሆን አማራጭም ተቀምጧል። አዲስ የኮሮናቫይረስ አይነት የሚስተዋል ከሆነ አባል አገራት በፍጥነት የጉዞ ፈቃዶችን ለማስተካከል እድል ይኖራቸዋል። ይህ ሁኔታም በየሁለት ሳምንቱ ይገመገማል ተብሏል።

አባል አገራቱ በአዲሱ የጉዞ እቅድ ላይ ዛሬ ማክሰኞ ዕለት ውይይት ማድረግ እንደሚጀምሩ ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ የአውሮፓ ሕብረት ዲጂታል የምስክር ወረቀት ለመጠቀም ማሰቡንም አስታውቋል።

የምስክር ወረቀቱ ተጓዦች ከኮቪድ-19 የሚከላከል ክትባት ስለመውሰዳቸው፣ ተመርምረው ኮሮናቫይረስ እንደሌለባቸው አልያም ከዚህ በፊት በቫይረሱ ተይዘው በቅርቡ ያገገሙ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚችል ነው።

በእቅዱ መሰረት የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ከሕብረቱ ውጪ ከሆኑ አገራት የሚመጡ ጎብኚዎችን በተቀመጡት መስፈርቶች ሰመረት እየተቀበሉ ማስተናገድ ይችላሉ ማለት ነው።

ተጨማሪም ክትባቱን ማግኘት ያልቻሉ ህጻናት ተመርምረው ቫይረሱ እንደሌለባቸው እስከተረጋገጠ ድረስ ከወላጆቻቸው ጋር አብረው መጓዝ ይችላሉ። ነገር ግን አውሮፓ ከገቡ በኋላ ተጨማሪ ምርመራ ሊጠብቃቸው ይችላል ተብሏል።

እቅዱ በአሁኑ ሰአት አውሮፓ ውስጥ ተግባራዊ እየሆኑ ያሉ ሕጎችን የማይጣረስ ሲሆን የሕበረቱ አባል አገራት ዜጎችና ለረጅም ዓመታት እዛ የኖሩ ሰዎችን አይመለከትም።

አዲሱ እቅድ ከአየርላንድ፣ አይስላንድ፣ ሌንቸስታይን፣ ኖርዌይ እና ሰዊዘርላንድ ውጪ ሁሉንም የአውሮፓ ሕብረት አገራት ያካተተ ነው።

እስካሁን ድረስ የአውሮፓ ሕብረት ለአራት ክትባቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቃድ ሰጥቷል። እነዚህም ፋይዘር፣ ሞደርና፣ አስትራ ዜኔካ እና ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ናቸው። ከጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ውጪ ሌሎቹ ክትባቶች ለከፍተኛ የመከላከል አቅም ሲባል ሁለት ጊዜ መከተብ ያስፈልጋቸዋል።