ኮቪድ-19: በእስራኤል ለመጀመሪያ ጊዜ ለተከታታይ 10 ወራት ሞት አልተመዘገበም

ታትሟል

ፈጣን የክትባት ዘመቻ እያካሄደች ያለችው እስራኤል ለ10 ተከታታይ ወራት በኮቪድ-19 ምክንያት ሞት አለመመዝገቧን አስታወቀች።

በአገሪቱ በኮሮናቫይረስ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች አሃዝ 6ሺህ 346 ሆኖ ሳይቀየር ለወራት መዝለቁን የእስራኤል ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

በእስራኤል በጥር ወር ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረው የወረርሽኙ ስርጭት አሁን ላይ ቅናሽ አሳይቷል።

የኮቪድ-19 ክትባት በሰፊው መሰጠቱን ተከትሎ የእስራኤል መንግሥት የእንቅስቃሴ ገደቦችን እያላላ ይገኛል።

በርካታ ዜጎቻቸውን ከከተቡ አገራት መካከል እስራኤል ተጠቃሽ ናት። እስከ ሐሙስ ብቻ አምስት ሚሊዮን የኮቪድ -19 ክትባቶችን ሰጥታለች።

ዘጠኝ ሚሊዮን ገደማ ከሚሆነው የሃገሪቱ ህዝብ ቁጥር ከ53 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሁለት ዙር ክትባቶችን እንደወሰዱ የጤና ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

ሚኒስትሩ ጁሊ ኤደልስቴይን አርብ ዕለት በትዊተር ገጻቸው "ይህ ለጤናው ስርዓት እና ለእስራኤል ዜጎች ትልቅ ስኬት ነው። በጋራ የኮሮናቫይረስን እናጠፋለን" ብለዋል።

በእስራኤል ትልቅ በሆነው የሼባ ሕክምና ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ኤያል ሌሸም እንዳሉት አገሪቱ ወደ "ሄርድ ኢሙኒቲ" ልትደርስ ተቃርባለች ብለዋል።

ከፍተኛ መጠን ያለው ሕዝብ በሽታውን የመከላከል አቅም ሲያዳብሩ የቫይረሱ ስርጭት ይገታል፤ ይህም 'ሄርድ ኢሙኒቲ' ይባላል።

የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያዎች 'ሄርድ ኢሙኒቲ' ደረጃ ላይ ለመድረስ አገራት ከ65-70 በመቶ የሚሆነው ሕዝባቸውን መከተብ ይኖርባቸዋል ይላሉ።

ተጨማሪ ገደቦች መነሳታቸውን ተከትሎ በእስራኤል የቫይረሱ ስርጭት መቀነስ ብቸኛው ምክንያት 'ሄርድ ኢሙኒቲ' ነው ብለዋል ሌሸም።

እስራኤል ፋይዘር እና ባዮንቴክ የተሠራውን እና ሁለት ጊዜ የሚሰጠውን ክትባት እየሰጠች ነው። የእስራኤል ጤና ሚኒስቴር በየካቲት ወር እንደገለጸው ሁለቱንም ዙር የፋይዘር ክትባት በወሰዱ ሰዎች ላይ የቫይረሱ ህመም በ95.8 በመቶ ቀንሷል።