ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ የአሜሪካ የጤና ባለሥልጣናት የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የኮቪድ-19 ክትባት እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ
የአሜሪካ የጤና ባለሥልጣናት እጅግ በጣም አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ሰዎች ላይ የደም መርጋት ችግር መታየቱን ተከትሎ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የኮቪድ-19 ክትባት እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ።
የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስሥልጣን (ኤፍዲኤ) ክትባቱ እንዲቆም ጥሪ የቀረበው ለጥንቃቄ ሲባል መሆኑን አስታውቋል።
ባለሥልጣኑ ከ6.8 ሚሊየን ብልቃጥ በላይ ክትባት ውስጥ የከፋ የደም መርጋት ችግር ያጋጠማቸው ስድስት ሰዎች ብቻ ናቸው ብሏል።
ይህ ሃሳብ የቀረበው ተመሳሳይ ችግር ያጋጠመው የኦክስፎርዱ አስትራዜኒካ ክትባትን ተከትሎ ነው።
የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን በትዊተር ገጹ ባሰፈረው ተከታታይ መልዕክት ባለሥልጣኑና የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) የተመዘገቡት ስድስት የደም መርጋት ችግሮችን እየተመለከተ መሆኑን ገልጿል።
ስድስቱ ግለሰቦች ክትባቱን ከወሰዱ በኋላ እምብዛም ያልተለመደ እና የከፋ የደም መርጋት ችግር አጋጥሟቸዋል ብሏል በመልዕክቱ።
"አሁን ላይ እነዚህ አሉታዊ ክስተቶች በጣም ጥቂት ናቸው" ሲልም አክሏል።
በመሆኑም "ለጥንቃቄ ሲባል ይህንን ክትባት መጠቀም ለጊዜው መቆም እንዳለበት እንመክራለን" ሲል አሳስቧል።
አክሎም ይህ አሉታዊ ክስተት ሊያጋጥም እንደሚችል የጤና ባለሙያዎች ማወቃቸውን ለማረጋገጥም ነው ብሏል።
ኤፍዲኤ እና ሲዲሲ ባወጡት የጋራ መግለጫ ያጋጠመው የደም መርጋት አንጎል ውስጥ የሚከሰት የደም መርጋት(ሲቪኤስቲ) መሆኑን አስታውቀዋል።
ተቋማቱ እንዳሉት ይህ ዓይነት የደም መርጋት ከተለመደው ውጭ የተለየ ሕክምና የሚያስፈልገው ነው።
የተለመደው ሕክምና ሄፓሪን የተባለ የደም መርጋትን የሚከላከል መድኃኒት ሲሆን ይህ ግን "አደገኛ ሊሆን ይችላል" ሲሉ አማራጭ መድኃኒት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ሁሉም የደም መርጋት ያጋጠማቸው ግለሰቦች ከ18 እስከ 48 የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሴቶች ናቸው። እነዚህ ሴቶች ምልክቱን ያዩት ከተከተቡ በኋላ ከስድስት እስከ አስራ ሦስት ባሉት ቀናት ውስጥ ነው።
ኒው ዮርክ ታይምስ የአንዷ ሴት ሕይወት እንዳለፈና ሌላኛዋ በኔብራስካ ግዛት ውስጥ በአስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ዘግቧል።
ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት
ኤፍዲኤ እና ሲዲሲ በጋራ ባወጡት መግለጫ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት የወሰዱ ሰዎች በተከተቡ በሦስት ሳምንታት ውስጥ ከባድ ራስ ምታት፣ የሆድ ህመም፣ የእግር ህመም ወይም የትንፋሽ ማጠር ካጋጠማቸው የጤና ባለሙያ ማማከር እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የአሜሪካ የጤና ኩባንያ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን በበኩሉ ደኅንነት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ በመግለፅ፤ የጤና ባለሥልጣናቱ ያወጡትን ያጋጠመ አሉታዊ ክስተት እንደተጋራው ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
አክሎም "አነስተኛ የፕላትሌት መጠን ያላቸውን ጨምሮ የደም መርጋት ችግር ያጋጠማቸው ሰዎች ከኮቪድ 19 ክትባት ጋር ተያይዞ ሪፖርት መደረጉን እናውቃለን። በአሁኑ ሰዓት፤ ይህ በቁጥር እጅግ አነስተኛ የሆነ የደም መርጋት ችግር፤ ከጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት ጋር የሚያገናኘው ነገር ስለመኖሩ የሚያሳይ ግልፅ የሆነ ማስረጃ የለም" ብሏል።
ነገር ግን ከመድኃኒት ተቆጣጣሪዎቹ ጋር በቅርበት መስራቱን እንደሚቀጥል ኩባንያው ገልጿል።
አስትራዜኔካ ክትባት
ከአስር ሚሊየን በላይ ለሚቆጠሩ ሰዎች የተዳረሰው የኦክስፎርዱ አስትራዜኔካ ክትባት አልፎ አልፎ በተከተቡት ላይ የደም መርጋት ችግር እንዳጋጠመ ታይቷል።
ይህንንም ተከትሎ አንዳንድ አገራትን ክትባቱ እንዳይሰጡ አድርጓቸው የነበረ ቢሆንም አብዛኞቹ ክትባቱን እንደገና መስጠት ጀምረዋል።
ይሁን እንጂ አንዳንድ አገራት ክትባቱን ለመስጠት የእድሜ ገደብ አስቀምጠዋል። ለምሳሌ ጀርመን ይህንን ክትባት ከ60 ዓመት በላይ ለሆናቸው ሰዎች እንዲሰጥ ወስናለች።
የዩናይትድ ኪንግደም ባለሥልጣናት ደግሞ ከ30 ዓመት በታች የሆናቸው አማራጭ ክትባት እንዲሰጣቸው መክረዋል።