ጉዳፍ ፀጋይ የ1500 ሜትር የቤት ውስጥ ሩጫ የዓለም ክብረ ወሰንን አሻሻለች

ጉዳፍ ጸጋይ

የፎቶው ባለመብት, worldathletics

ታትሟል

ጉዳፍ ፀጋይ ፈረንሳይ ሌቪን በተካሄደው የ1500 ሜትር የቤት ውስጥ ሩጫ የዓለም ክብረ ወሰንን በማሻሻል አሸነፈች።

ኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ፀጋይ የዓለም ክብረ ወሰን በ2 ሴኮንድ በማሻሻል 3፡53፡09 በሆነ ሰዓት ውድድሩን አጠናቃለች።

ጉዳፍ ያሻሻለችው ክብረ ወሰን በሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ገንዘቤ ዲባባ በ2014 (እአአ) ካርልስሩሄ ላይ የተያዘ ነበር።

"የዓለምን የቤት ውስጥ ሩጫ ክብረ ወሰን በማሻሻሌ እጅግ ደስተኛ ነኝ" ያለችው አሸናፊዋ ጉዳፍ፤ "ጠንከራ ልምምድ ሰርቼ ስለነበር የዓለምን ክብረ ወሰን ለመስበር ራሴን አዘጋጅቼ ነበር" ብላለች።

ትናንት ምሽት በወንዶች በተደረገ የ3 ሺህ ሜትር የቤት ውስጥ ሩጫም ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎቻቸውን በፍጹም የበላይነት አሸንፈዋል። ኢትዮጵያውያኑ ከአንድ እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘው ሲያጠናቅቁ የዓለም ሁለኛው ፈጣን ሰዓትም በውድድሩ ተመዝግቧል።

በመሰናክል ሩጫ ጌትነት ዋለ በ3 ሺህ ሜትር ሩጫ በአንደኝነት ሲያሸንፍ ሦስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ተከታትለው በመግባት ድሉን አድምቀውለታል።

ሩጫውንም በ7፡24፡98 በሆነ ሰዓት በማጠናቀቅ የወርቅ ተሸላሚ ሆኗል። ጌትነት የገባበት ሰዓት የዓለም ሁለተኛው ፈጣን ሰዓትም ሆኖ ተመዝግቦለታል።

የ20 ዓመቱ ጌትነት ለረጅም ጊዜ ክብረወሰኑን 7፡24፡90 በሆነ ሰዓት ለያዘው ዳንኤል ኮሜን ትልቅ ስጋት ፈጥሯል።

የዓለም ሻምፒዮና የ5 ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ አሸናፊው ሰለሞን ባረጋ ደግሞ በእዚሁ ወድድር 7፡26.10 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆኖ አጠናቅቋል።

ለሜቼ ግርማ በ7፡27፡98 ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ በሪሁ አረጋዊ ደግሞ በ7፡29፡24 አራተኛ በመሆን ውድድሩን ጨርሷል።

ከአሁን በፊት በ3 ሺህ ሜትር ሜትር የቤት ውስጥ ሩጫ ከ00፡07፡30 በታች መግባት የቻሉት 6 ሯጮች ብቻ ነበሩ። አሁን ግን እድሜያቸው ከ19 እስከ 21 የሆኑ አራት ሯጮች ከ00፡07፡30 በታች ይህንን ውድድር ማጠናቀቅ ችለዋል።

ይህም ክብረወሰኑን በቅርቡ ለማሻሻል ተስፋ የታየበት ነው ተብሏል።