ኃይማኖት፡ ኢንዶኒዢያ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሒጃብ ግዴታ እንዳይሆን ወሰነች

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
ከዓለም በርካታ የእስልምና እምነት ተከታይ ያላት አገር ኢንዶኒዢያ በትምህርት ቤቶቿ ውስጥ ሒጃብና ኢስላማዊ አለባበስ በአጠቃላይ ግዴታ እንዳይሆን አዘዘች፡፡
እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው በበርካታ የኢንዶኒዢያ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ሙስሊም ያልሆኑ ተማሪዎች በግዴታ ሒጃብ እንዲለብሱ እንደሚደረጉ ከተደረሰበት በኋላ ነው፡፡
ሙስሊም ያልሆኑ ተማሪዎች በዚህ ረገድ የሚደርስባቸውን በደል የሚያትት ዘገባ በማኅበራዊ ሚዲያ ተሰራጭቶ ቅሬታን ከፈጠረ በኋላ ነው አገሪቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ተብሏል፡፡
‹‹ኢስላማዊ አለባበስ የግለሰቦች ምርጫ ነው፡፡ የትምህርት ቤቶች ውሳኔ መሆን የለበትም›› ብለዋል የኢንዶኒዢያ የትምህርትና ባሕል ሚኒስትር ናዲያም መካሪም፡፡
መንግሥት ለሁሉም ትምህርት ቤቶች የ30 ቀናት የዝግጅት ጊዜን ሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህ አንድ ወር ውስጥ ትምህርት ቤቶቹ ኢስላማዊ አለባበስን የሚያስገደድ ደንብ ካላቸው ያን መሠረዝ ይኖርባቸዋል፡፡
ለዚህ መመርያ ተገዢ በማይሆኑ ትምህርት ቤቶች ላይ መንግሥት የማያዳግም እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል፡፡
በፓዳንግ በሚገኝ አንድ የሙያ ትምህርት ቤት ውስጥ አንዲት ሙስሊም ያልሆነች ተማሪ በተደጋጋሚ ሒጃብ እንድትለብስ ጫና ተደርጎባት አሻፈረኝ ማለቷን ተከትሎ ነው ይህ ጉዳይ በኢንዶኒዢያ መነጋገርያ የሆነው፡፡
ተማሪዋ ግን በፍጹም አላደርገውም በሚል ከጸናች በኋላ ወላጅ እንድታመጣ ተደርጎ ትምህርት ቤቱና ወላጆቿ ሊግባቡ አልቻሉም፡፡
የልጅቷ አባት ለቢቢሲ የኢንዶኒዢያ ወኪላችን እንደተናገሩት ልጃቸው ሁልጊዜም በዚህ ጉዳይ እንግልት ይደርስባት ነበር፡፡ ‹‹አስተዳዳሪዎች ሁልጊዜ ቢሮ እያስጠሩ ጫና ይፈጥሩባታል፡፡ የሷ ምላሽ እኔ ሙስሊም አይደለሁም፤ ሒጃብ ለምን እለብሳለሁ የሚል ነበር›› ብለዋል አባት ኢሊያኑ ሃይኢ፡፡
‹‹የታለ የኃይማኖት ነጻነቴ ታዲያ? ይህ የሕዝብ ትምህት ቤት ነው፡፡ ልጄን ሒጃብ እንድትለብሳት ካስገደድኳትማ ማንነቷን ነጠቅኳት ማለት ነው›› ብለዋል የልጂቱ አባት ለቢቢሲ።
የልጅቷ ወላጆች ከትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች ጋር የተነጋገሩትን ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ካሰራጩት በኋላ የሒጃብ ጉዳይ በመላው አገሪቱ አዲስ መነጋገርያ ሆኗል፡፡
በዚህ ቪዲዮ የትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች ሴቶች ሁሉም ሒጃብ እንዲለብሱ የትምህርት ቤቱ ሕግ እንደሚያስገደድ ሲናገሩ ይታያሉ፡፡
ነገሩ ለሕዝብ ከተሰራጨ በኋላ ጉዳዩ የፖለቲካ ውይይትን ፈጥሯል፡፡
በመጨረሻ ግን የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን ከዚህ በኋላ ተማሪዎች እንደ እምነታቸው ምርጫ ብቻ እንዲለብሱ እንደሚደረግና ሒጃብም ግዴታ እንደማይሆንባቸው አረጋግጠዋል፡፡
የኢንዶኒዢያ የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትር ያቁት ቾሊሊ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ‹‹ሃይማኖት ግጭትን የሚያፋፍም አይደለም፡፡ ሃይማኖት የተለዩ ሰዎችን ማግለልና መበደልንም አይፈቅድም›› ሲሉ ክስተቱን አውግዘዋል፡፡
የሂይማን ራይትስ ዎች ተመራማሪ አንድሪያስ ሃርሶኖ ለሮይተርስ እንደተናገሩት ኢንዶኒዥያ የሴቶችን መብት ለማክበር መቁረጧን አድንቀው አሁንም ቢሆን ግን በ20 አውራጃዎች ውስጥ ሒጃብን በትምህርት ቤቶች ግዴታ የሚያደርጉ ደንቦች መኖራቸውን አስታውሰዋል፡፡
ኢንዶኒዢያ በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የእስልምና እምነት ተከታይ ያለባት ቁጥር-1 አገር ናት፡፡ ነገር ግን ከእስልምና ሌላ ሌሎች 6 ሃይማኖቶች በአገሪቱ እውቅና አላቸው፡፡ የሃይማኖት ብዝሃነትን የሚያስተገናግድና ፓንካሲላ የሚባል የአገሪቱ ፍልስፍና የእምነት ነጻነትን የሚያቀዳጅ ነው፡፡












