የአሜሪካ ሕዝብ እንደራሴዎች 'አክራሪዋን' የምክር ቤት አባል ለማስወገድ ድምፅ ሰጡ

ታትሟል

የዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ እንደራሴዎች አክራሪዋን የሪፐብሊካን ፓርቲ አባል ከሁለት ኮሚቲዎች ለማስወገድ ድምፅ ሰጡ።

ማርጆሪ ግሪን የተሰኙት የምክር ቤቱ አባል መሠረት የሌላቸው የሴራ ትንተናዎችን በማሰራጨት ይታወቃሉ።

አልፎም እንደራሴዋ ዴሞክራቶች ላይ በሚሰንዝሯቸው ጠብ አጫሪ አስተያየቶቻቸውም ይታወቃሉ።

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ሁሉም ዴሞክራቶች ሴትዬዋ ከኮሚቴ አባልነታቸው ይነሱ ብለው ድምፅ ሲሰጡ፣ 11 ሪፐብሊካኖችንም አብረዋል።

በአጠቃላይ 230 ለ199 በሆነ ድምፅ የአሜሪካ ሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ሴትዬዋን ለመቅጣት ወስኗል።

አሜሪካ ውስጥ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና የ9/11 የሽብር ጥቃት የተቀነባበረ ነው ብለው የሚያምኑት እንደራሴዋ፣ ድምፅ ከመሰጠቱ በፊት ባደረጉት ንግግር ይህ ድርጊታቸው የሚያስወቅሳቸው እንደሆነ አልካዱም።

በአሜሪካ ፖለቲካ መሰል ክስተቶች እምብዛም አይስተዋሉም። ብዙ ጊዜ አባላት አልባሌ ድርጊት ሲፈፅሙ ፓርቲው ነበር የሚቀጣቸው።

እንደራሴዋ ድርጊታቸው የሚያስኮንናቸው እንደሆነ ይናገሩ እንጂ ይቅርታ ከመጠየቅ ተቆጥበዋል። እነዚህ ድርጊቶች የሕዝብ ተወካይ ከመሆኔ በፊት የፈፅምኳቸው ናቸው ሲሉም ተከራክረዋል።

"እኒህ ያለፉ ድርጊቶች ናቸው። እነዚህ ነገሮች እኔን አይወክሉኝም" ብለዋል እንደራሴዋ በባልደረቦቻቸው ፊት ቀርበው ባደረጉት ንግግር።

የ46 ዓመቷ የግዛተ ጆርጂያ ተወካይ የሴራ ትንተና ከሚያራምዱ እኩል መገናኛ ብዙሃንም ውሸትን በማራገብ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።

ማርጆሪ ማናቸው?

ሴትዬዋ በበይነ መረብ ዓለም እጅግ ታዋቂ ናቸው። ማሕበራዊ ድር አምባዎች ላይ በንቃት ይሳተፋሉ። የዶናልድ ትራምፕ ቀንደኛ ደጋፊ ናቸው።

አንድ ፌስቡከኛ የአሜሪካ ሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ "ጭንቅላታቸውን በጥይት ይመቱ" ብሎ የለጠፈውን መልክት በመውደዳቸው [ላይክ በማድረጋቸው] ምክንያት ብዙ ወቀሳ አስተናግደዋል።

"ባራካ ኦባማ ይሰቀሉ" የሚል መልዕክት ሥር ገብተው ደግሞ "መድረኩ ተዘጋጅቷል" ሲሉ ኮምተው ነበር።

ከአንድ ጅምላ ግድያ ያመለጠን ታዳጊ መንገድ ላይ አግኝተው 'አውሬ' ብለው ሲስደቡት የሚያሳይ ምስል ተለቆ አጃኢብ አሰኝቶ እንደነበር አይዘነጋም።

በፈረንጆቹ 2018 ደግሞ በየሁለት ዓመቱ የሚደረገው የአሜሪካ የምክር ቤት ምርጫ "መንግሥታችን በሙስሊሞች እንዲወረር እያደረገ ነው" የሚል አስተያየት ሰንዝረው ነበር።

ማርጆሪ በቅርቡ የተደረገውን የአሜሪካ ምርጫ ያሸነፉት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው ብለው ያምናሉ።

እንደራሴዋ ባደረጉት ንግግር ስለነዚህ ጉዳዮች አንዳችም ነገር አላሉም።