ካረጁ የቤት እቃዎች ምን ያህሉን በድጋሚ ይጠቀማሉ?

ፈረንሳይ የሚኖረው ብሩኖ ሞቲስ በጎ ፍቃደኛ እቃ ጠጋኝ ነው።
በሚኖርበት ከተማ በራሳቸው ተነሳሽነት ቁሳቁስ የሚጠግኑ ሰዎች የሚሠሩባቸው ካፌዎች ብዙ ናቸው። በየወሩ በነጻ የተበላሹ የቤት ውስጥ መገልገያዎችን ይጠግናሉ።
ይህን አገልግሎት የጀመረው ማርቲን ፖስትማ የተባለ ጋዜጠኛ እአአ በ2009 አምስተርዳም ውስጥ ነበር። ሐሳቡ ወደተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ተስፋፍቷል።
ፓሪስ ውስጥ የጥገና ካፌ የሚያስተባብረው ኢማኑኤል ቫሌ "ብዙ ቁሳቁስ የምናበዛና ተረፈ ምርት የምናከማች ማኅበረሰብ ነን" ይላል።
እአአ በ2016 የመላው ዓለም የኤሌክትሮኒክስ ተረፈ ምርት 45 ሚሊዮን ቶን ደርሶ ነበር።
የተጣለው ያረጀ ስልክ፣ ኮምፒውተር፣ የቤት ውስጥ መገልገያ ወዘተ. . . 62.5 ቢሊዮን ዶላር ያወጣል። ከተረፈ ምርቱ መካከል በድጋሚ ጥቅም ላይ የዋለው 20 በመቶው ብቻ ነው።
ይህ ችግር አውሮፓ ውስጥ ጎልቶ ይስተዋላል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውሉ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ከ12% እስከ15% ብቻ ናቸው።
የኤሌክትሮኒክስ ተረፈ ምርት (ኢ ዌስት) በሕገ ወጥ መንገድ ከምዕራቡ ዓለም ወደተቀረው የዓለም ክፍል ይጣላል።
ፊሊፒንስ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ እና ቻይና በ2021 መጨረሻ 52 ሚሊዮን ቶን ተረፈ ምርት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል።
የኤሌክትሮኒክስ ተረፈ ምርት በድጋሚ ጥቅም ላይ ሳይውሉ ከሚጣሉ የተረፈ ምርት አይነቶች በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
ይህም በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው። በተረፈ ምርት ሳቢያ የካርቦን ልቀት ይጨምራል። የውሃ አካላትም ይበከላሉ።
ተረፈ ምርትን ማስቀረት ከሚቻልበት መንገድ አንዱ ቁሳቁሶችን በድጋሚ ጥቅም ላይ ማዋል ነው። ቁሳቁሶች ቢያረጁም ጠግኖ መጠቀምም ይመከራል።
አምና ፈረንሳይ ያጸደቀችው ሕግ ቁሳቁሶች ከመጣላቸው በፊት በድጋሚ ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችሉ ይፈትሻል።
ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ ቴሌቭዥን ወይም ሌላ ኤሌክትሮኒክስ መጠገን የሚችል ከሆነ በድጋሚ አገልግሎት ላይ ይውላል ማለት ነው።
መንግሥት በቀጣይ አምስት ዓመታት የኤሌክትሮኒክስ ጥገናን በ60 በመቶ ማሳደግ ይፈልጋል።
አንድ እቃ በድጋሚ ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችል የሚመዘነው በተለያየ መስፈርት ነው። አንደኛው እቃው መጠገን ይችላል? የሚለው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ መለዋወጫ የማግኘት ጉዳይ ነው።
ፈረንሳይ ይህንን ሕግ የማያከብሩ ተቋሞችን እስከ 13 ሺህ 300 ዶላር ትቀጣለች።
አንድ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም እንደሚለው፤ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ቁሳቁሶችን በድጋሚ ጥቅም ላይ ማዋል በከፍተኛ ሁኔታ ብክለትን ይቀንሳል።
አንዳንድ ባለሙያዎች ቁሳቁስን በድጋሚ ጥቅም ላይ ማዋል የመኪና ቁጥርን ከመቀነስ ያልተናነሰ ጥቅም እንዳለው ያምናሉ።
ቁሳቁስ አለመጣልን የሚያበረታታ ሕግ ካላቸው መካከል አውስትራሊያን መጥቀስ ይቻላል። በጥገና ዘርፍ የተሰማሩ ከተጨማሪ እሴት ታክስ 10% ይቀነስላቸዋል።
ሀንጋሪ ውስጥ ደግሞ ቁሳቁሶች ጥቅም የሚሰጡበት የጊዜ ገደብ እንዲራዘም ይደረጋል።
ጥገናን የሚያበረታታ ንቅናቄ አባል የሆነችው ክሎይ ሚኮጃዝክ እንደምትለው፤ አምራች ድርጅቶችም ቁሳቁስን በድጋሚ ጥቅም ላይ ማዋልን ከግምት በማስገባት ማምረት ይጠበቅባቸዋል።
ለምሳሌ ስልኮችን ከመጣል ይልቅ በየጊዜው መተግበሪያዎችን እያደሱ ለረዥም ጊዜ መጠቀም አንድ አማራጭ ነው። ስለዚህ የቴክኖሎጂ ተቋሞች ይህንን አሠራር ቀላል ማድረግ አለባቸው።
አንዳንድ ስልክ አምራቾች በየጊዜው የሚያወጡት ስልክ እንዲሸጥ ሲሉ የቀደሙ ስልኮች ታድሰው ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማድረጋቸው ይተቻል።
ክሎይ እንደምትለው አምራቾች ጥገናን ቀላል ማድረግ አለባቸው። ጥገና ርካሽና በቀላሉ የሚገኝ ከሆነ ተጠቃሚዎችን እንደሚያበረታታም ታምናለች።












