ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሌባኖስ የተቃውሞ ሠልፍ ለአራተኛ ቀን ተካሄደ
የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የታወጀውን የእንቅስቃሴ ገደብ በመቃወም ሌባኖሳዊያን የመንግሥት ሕንጻዎችን አጋዩ።
ለአራተኛ ተከታታይ ቀናት በቀጠለው ተቃውሞ የመንግሥት መስሪያ ቤት ሕንጻዎች ትሪፖሊ በተሰኘች ከተማ ተቃጥለዋል።
ትናንት በተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ የጸጥታ አስከባሪዎች ከሰልፈኞች ጋር ተጋጭተው ከ100 በላይ ሰዎች መጎዳታቸውን የሌባኖስ ቀይ መስቀል አስታውቋል።
በምጣኔ ሃብት ቀውስ ውስጥ በምትገኘው ሌባኖስ በርካታ ወጣቶች ሥራ አጥ ሆነው ሳለ መንግሥት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የእንቅስቃሴ ገደብ ማወጁን ከፍተኛ ተቃውሞን ቀስቅሷል።
መንግሥት ባስተላለፈው ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ፤ መሠረታዊ ሠራተኞች እስካልሆኑ ድረስ ሰዎች ከቤታቸው መውጣት አይችሉም። የሌባኖስ መንግሥት መሠረታዊ ሠራተኛ የሚላቸው ሃኪሞች፣ የአስቸኳይ ጊዜ ሰራተኞች እና የመሳሰሉትን ነው።
7 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት ሌባኖስ በአሁኑ ወቅት አንድ ሦስተኛው ሥራ አጥ ሲሆን ከጠቅላለው ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ከድህነት ወላል በታች እንደሚኖር ይገመታል። በአገሪቱ ላይ የዋጋ ግሽበትም በሶስት እጥፍ መጨመሩ ተገልጿል።
ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ በሌባኖስ መዲና ቤይሩት የደረሰው ፍንዳታ ከ200 በላይ ሰዎችን ከመግደሉም በተጨማሪ 4.6 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት አውድሟል።
ከዚህ በተጨማሪም ከጎረቤት አገር ሶሪያ ተፈናቅለው ሌባኖስ የከተሙ 860ሺህ ተፈናቃዮች ለመንግሥታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሌላ ጫናን ስለመፍጠሩ ይነገራል።
ይህ መንግሥት ይፋ ያደረገው የእንቅስቃሴ ገደብ አዋጅ የታወጀው ጥር 14 ሲሆን እስከ የእንቅስቃሴ ገደቡ እስከ የካቲት 1 ይዘልቃል።
የአገሪቱ መንግሥት የጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ በአገሪቱ ጤና ስርዓት ላይ ጫና እንዳይፈጥር ይረዳል ይላል። ይሁን እንጂ በሌባኖስ የሚገኙ ሆስፒታሎች የጽኑ ሕሙማን ክፍላቸው 94 በመቶ በታማሚዎች እንደተያዘ ሪፖርት አድርገዋል። የመድሃኒት እጥረት መኖሩም ሪፖርት ተደርጓል።
እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አሃዝ ከሆነ ከ300ሺህ በላይ ሰዎች በሌባኖስ በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 2ሺህ 600 የሚሆኑት ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው አልፏል።