ሩስያ የተቃውሞ ሰልፉን ተከትሎ ቲክቶክን ልትቀጣ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሩስያ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ ቲክቶክን እንደምትቀጣ አስታወቀች።
በማኅበራዊ ሚዲያ ወጣቶችን ለተቃውሞ የሚያነሳሱ መልዕክቶች ሲተላለፉ ቲክቶክ ሳያጠፋቸው በመቅረቱ ነው ቅጣቱ የተጣለበት።
ቲክቶክ፣ ትዊተር እና ፌስቡክ ጽሑፎችን እንዳላጠፉና ከሩስያ መንግሥት ጋር እንዳልተባበሩ የአገሪቱ የሚዲያ ተቆጣጣሪ ተናግሯል።
ቅጣቱ እስከ 53,000 ዶላር ሊደርስ ይችላል።
ሰልፉ የተካሄደው ተቃዋሚው አሌክሲ ናቫልኒ ከእስር እንዲፈታ ለመጠየቅ ነበር።
የፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቀንደኛ ተቀናቃኝ ናቫልኒ ከጀርመን ወደ ሩስያ ከተመለሰ በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወሳል።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሩስያውያን የፖሊስን ትዕዛዝ ተላልፈው በተቃውሞው ተሳትፈዋል። ተቃውሞውን በማስተባበር ከፍተኛ ሚና የተጫወተው ደግሞ ማኅበራዊ ሚዲያ ነበር።
ሰልፍ እንዲካሄድ የሚያነሳሱ ቪድዮዎችን በመቶ ሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች ቲክቶክ ላይ ተመልክተዋል።
የሩስያ ሚዲያ ተቆጣጣሪ ሮስኮምኣዶዘር፤ ቲክቶክ ቪድዮዎቹን እንዲያጠፋ ጠይቋል። የሚዲያ ተቆጣጣሪው ማኅበራዊ ሚዲያዎች "ታዳጊዎች በሰልፉ እንዲሳተፉ ሲጠራ መልዕክቱን አላጠፉም" ሲል ይከሳል።
ሩስያ ውስጥ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሰልፍ እንዲያካሂዱ ማነሳሳት ክልክል ነው።
በጸረ ሙስና ንቅናቄው የሚታወቀው የናቫልኒ ደጋፊዎች በዚህ ሳምንት መጨረሻም ሰልፍ ለማድረግ አስበዋል።
የማኅበራዊ ሚዲያ ተቋሞቹ ከሩስያ መንግሥት ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ሰልፍ የሚጠሩ ጽሑፎችን አላጠፉም።
እኒዚህ ጽሑፎች 170 እንደሆኑ የአገሪቱ የሚዲያ ተቆጣጣሪ ተናግሯል።
ፕሬዘዳንት ፑቲን ማኅበራዊ ሚዲያዎች "ከመንግሥት ጋር እየተፎካከሩ ነው" ሲሉ ተችተዋል።
በዓለም አቀፉ የምጣኔ ሀብት ጉባኤ ላይ በበይነ መረብ ባደረጉት ንግግር "ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ያላቸው ድርጅቶች ብቻ አይደሉም። ንግዳቸው ማኅበረሰብን መቆጣጠር ላይ የተመሠረተ ነው። ይህንን በአሜሪካም አይተነዋል" ብለዋል።
ከሩስያ መገናኛ ብዙሃን አብላጫውን ቁጥር የያዙት በመንግሥት የሚተዳደሩ ናቸው። ስለዚህም አንጻራዊ ነጻነት ያለው በማኅበራዊ ሚዲያና በሌሎች አገራት በሚተዳደሩ የዜና ተቋሞች ነው።
የሩስያ ባለሥልጣኖች በተቃዋሚው ናቫልኒ ስም ያሉ ቤቶችና ተቋሞችን አስፈትሸዋል። የጸረ ሙስና ቡድኑ ቢሮና የቤተሰቡ ቤት ብርበራ ከተደረገባቸው መካከል ይገኙበታል።
ባለቤቱ ዩሊያ "በሬን ሰብረው ነው የገቡት። ጠበቃዬ እንዲገባ አልፈቀዱም" ብላለች።
የሩስያ የአገር ውስጥ ሚንስትር ሰልፈኞቹ "ኮሮናቫይረስ እንዲሰራጭ መንገድ ከፍተዋል" ሲል ምርመራ ከፍቶባቸዋል።












