የታንዛኒያው ፕሬዝደንት የኮቪድ-19 ክትባት ለታንዛኒያውያን አያስፈልግም አሉ

ፕሬዝደንት ማጉፉሊ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝደንት ማጉፉሊ
ታትሟል

የታንዛኒያው ፕሬዝደንት ጆን ማጉፉሊ የአገሪቱ ጤና ባለስልጣናት የኮቪድ-19 ክትባቶችን ለመጠቀም ከመወሰናቸው በፊት ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው አሉ።

ማጉፉሊ ምንም አይነት ማረጋገጫ ሳያቀርቡ የኮቪድ-19 ክትባት ሕዝቡን ሊጎዳ ይችላል ብለዋል።

"የጤና ሚንስቴር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። ጥናቶችን ሳያከናውኑ እነዚህን ክትባቶች ለመሞከር መፍጠን የለባቸውም። ሁሉም ክትባት ለእኛ ጠቃሚ አይደሉም፤ መጠንቀቅ አለብን። መሞከሪያ መሆን የለብንም" ሲሉ ማጉፉሊ ተናግረዋል።

"ክትባቶች አደገኛ ናቸው። ነጩ ሰውዬ ክትባት አገኘሁ ካለ፤ ለኤድስ፣ ለካንሰር እና ለቲቢ እስካሁን ክትባት ሊኖረው ይገባል።"

ፕሬዝደንቱ ይህን ይበሉ እንጂ የኮቪድ-19 ክትባቶች ለሰው ልጆች እንዲሰጡ የተፈቀደው በርካታ ምርመሮች እና ሙከራዎች ከተከናወነባቸው በኋላ ነው።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ተሞክረው፣ ደህንነታቸው ተረጋግጦ፣ በመድሃኒት ተቆጣጣሪ አካላት ፍቃድ በማግኘታቸው ነው ለሰዎች እየተሰጡ ያሉት በማለት የቢቢሲ የጤና ጉዳዮች ዘጋቢ ፊሊፓ ሮክስቢይ ትናገራለች።

ፕሬዝደንት ማጉፉሊ ግን ዜጎቻቸውን ይህን ክትባት ከመውሰዳቸው በፊት ጥንቃቄ አድርጉ ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ከክትባት ይልቅ ጸሎት ማድረግ እና ለባህላዊ መድሃኒት ቅድሚያ መስጠት የተሻለ አማራጭ ነው ሲሉ ታንዛኒያውያንን መክረዋል።

"በርካታ አገራት የእንቅስቃሴ ገደቦችን አስተዋውቀዋል። በታንዛኒያ ግን የሰዎችን እንቅስቃሴ የመገደብ እቅድ የለንም። ፈጣሪያችን በሕይወት አለ፤ እርሱ ይጠብቀናል" ሲሉ ተደምጠዋል።

ፕሬዝደንት ማጉፉሊ ከወራት በፊት ታንዛኒያ ከኮቪድ-19 ነጻ ሆናለች ብለው ያወጁ ሲሆን፤ በከተሞች አከባቢ ስለጨመረው የሰዎች ሞት ቁጥር ላይ ግን ያሉት ነገር የለም።

ማጉፉሊ አባል የሆኑበት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ባወጣው መግለጫ ግን፤ ታንዛኒያ መጀመሪያ ላይ የቫይረሱን ስርጭት መቆጣጠር ቢቻላትም አሁን ላይ ግን የቫይረሱ ስርጭት እንደ አዲስ መስፋፋቱን አስታውቋል።

የታንዛኒያ ጤና ሚንስቴር በአገሪቱ በቫይረሱ የሚያዙ፣ የሚሞቱ እና የሚያገግሙ ሰዎች አሃዝን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ካቆመ ወራቶች አልፈዋል።