የኒው ዚላንዱ አይነት የመስጊድ ጥቃት ሊያደርስ የነበረው ታዳጊ በቁጥጥር ሥር ዋለ

ታትሟል

በሲንጋፖር መስጊድ ውስጥ ጥቃት ሊያደርስ አሲሮ ነበር የተባለው የ16 ዓመት ታዳጊ በቁጥጥር ሥር ዋለ። ታዳጊው በኒው ዚላንድ ክራይስትቸርች መስጊድ በደረሰው ጥቃት ተነሳስቶ መስጊድ ውስጥ ሰዎችን ሊገድል ነበር ተብሏል።

የክራይስትቸርች ጥቃት የደረሰበትን ቀን መታሰቢያ በማድረግ ሰዎችን በስለት ሲደግል በቀጥታ ለማስተላለፍ አቅዶ ነበር።

በዓለም አቀፉ የጸጥታ ስምምነት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በእድሜ ትንሹ ነው።

በክራይስትቸርች የተፈጸመው ጥቃት በኒው ዚላንድ ታሪክ እጅግ የከፋው ነው። 50 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ጥቃት ፈጻሚው የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።

የ16 ዓመቱ ተጠርጣሪ በስም ባይጠቀስም የሲንጋፖር ዜግነት ያለው፤ በሕንድ መሰረት ካለው ጎሳ እንደሚመዘዝ፤ በእምነቱ ፕሮቴስታንት እንደሆነና ጥቃቱን ለመፈጸም የተነሳሳው "ለእስልምና ካለው ጥላቻ እና ጥቃት የማድረስ ጽኑ ፍላጎት ስላለው ነው" ሲል የአገር ውስጥ ሚንስትር አስታውቋል።

የኒው ዚላንዱ ጥቃት በደረሰበት ቀን ጥቃቱን ለመሰንዘር ማሰቡ በኒው ዚላንዱ ጥቃት እንደተነሳሳ ማሳያ ነውም ተብሏል።

ታዳጊው እንደ ኒው ዚላንዱ ጥቃት አድራሽ ብሬንቶን ታራት የጦር መሳሪያ ለመጠቀም አስቦ አንደነበረና መግዛት ስላልቻለ ስለት ለመጠቀም መወሰኑ ተገልጿል።

ሲንጋፖር ጥብቅ የመሣሪያ ቁጥጥር ሕግ አላት።

የአገር ውስጥ ሚንስትር እንዳለው፤ ታዳጊው ወንጀሉን ከመፈጸሙ በፊት እንደሚታሰር ወይም ጥቃቱን ከሰነዘረ በኋላ በፖሊስ እንደሚገደል አስቦ ነበር።

"ለመሞት ዝግጁ ነበር። ድርጊቱን ለመፈጸም ያቀደው ብቻውን ነው" ሲሉ የአገር ውስጥ ሚንስትሩ ኬ ሻንሙጋም ተናግረዋል።