ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሕንድ የአርሶ አደሮች ተቃውሞን ተከትሎ 200 ሰዎች ታሰሩ
በሕንድ መዲና ደልሂ ትላንት የተካሄደ የአርሶ አደሮች ተቃውሞ ላይ የተነሳ ግጭትን ተከትሎ ፖሊስ 200 ሰዎችን ማሰሩ ተገለጸ።
በግብርናው ዘርፍ ሕግ ላይ የተደረጉ ለውጦችን በመቃወም አርሶ አደሮች ድምጻቸውን ማሰማት ከጀመሩ ቆይተዋል።
ደልሂ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ወደ ከተማዋ ማዕከል ለመግባት ሲሞክሩ ከፖሊሶች ጋር ተጋጭተዋል።
በግጭቱ አንድ ተቃዋሚ እንደሞቱና ከ300 በላይ የጸጥታ ኃይሎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።
የአርሶ አደሮቹ አመራሮች እንዳሉት ተቃውሞው ሰላማዊ እንዲሆን ቢታሰብም ጥቂቶች ወደ ነውጥ ወስደውታል። ሆኖም ግን ተቃውሞውን እንደሚገፉበት አስታውቀዋል።
የታሰሩት ሰዎች ነውጥ በማስነሳት፣ የሕዝብ ንብረት በማውደምና ፖሊሶች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ይከሰሳሉ።
እስካሁን 22 ፖሊሶች ቅሬታ አቅርበዋል።
የፖሊስ ኃላፊዎች ለሕንዱ ኤክስፕረስ ጋዜጣ "እያጣራን ነው ያሰርነው። ሬድ ፎርት አካባቢ ያሉ የደህንነት ካሜራዎችንም እየተመለከትን ነው" ብለዋል።
ሬድ ፎርት ተቃውሞው የተካሄደበት ደልሂ ውስጥ የሚገኝ ታሪካዊ ቦታ ነው። የሕንድ መንግሥት 15 ወታደራዊ ተቋሞችን በተቃውሞው ቦታ አሰማርቶ ነበር።
ተቃውሞው የተካሄደው ሕንድ ሕገ መንግሥት ያጸደቀችበትን ቀን የሚዘክር ክብረ በዓል ባከበረችበት እለት ነው።የአርሶ አደሮቹ ቡድን ሳምያኩታ ኪሳን ሞራክ ተቃውሞን በማስታከክ የተነሳውን ነውጥ አውግዞ "ይህ ተግባር የኛ አይደለም" ብሏል።
ቡድኑ አዲሱን የግብርና ሕግ መቃወሙን እንደሚቀጥልም ይፋ አድርጓል።
መንግሥት አዲሱ ሕግ ግብርናን ነጻ ያደርጋል ቢልም አርሶ አደሮች ግን ወደ ድህነት ይከተናል በማለት ይቃወሙታል።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ሕጉን እየተቃወሙ ነው። ባለፈው ሳምንት መንግሥት ለውጡን ለማዘግየት ቢወስንም አርሶ አደሮቹ አልተቀበሉትም።
አርሶ አደሮቹ ተቃውሞ ሲያካሂዱ ከክብረ በዓሉ ጋር እንዳይጋጭ አማራጭ ተቃውሞ ማከናወኛ ጎዳናዎች ተሰጥተው ነበር።
ትራክተር በመንዳት ተቃውሟቸውን ያሰሙት አርሶ አደሮች ወደ ሬድ ፎርት ሲያቀኑ ነውጥ ተነሳ።
ፓሊሶች ተቃዋሚዎችን ከሬድ ፎርት ማስወጣትም ጀመሩ። ፖሊሶች አስለቃሽ ጭስ እንደተጠቀሙና የጸጥታ ኃይሎች ላይ በእንጨትና በብረት ጥቃት ያደረሱ እንደነበሩም ተገልጿል።
አዲሱ ሕግ የግብርና ምርቶች ዋጋና አሻሻጥን ያላላል። ለዓመታት የቆየ ሕግ የሕንድ አርሶ አደሮችን ከነጻ ገበያ ተከላክሎ ነበር።
አርሶ አደሮች አዲሱ ሕግ የዋጋ ተመንን በመሻር ለብዝበዛ ያጋልጠናል ብለው ይሰጋሉ። መንግሥት ሕጉን ቢያሞግስም አርሶ አደሮች "የሞት ፍርድ" ሲሉ ይገልጹታል።