የግድያ ዛቻ የደረሰበት የ11 ዓመቱ የመብት ተሟጋች

የፎቶው ባለመብት, FRANCISCO VERA
የ11 ዓመቱ ፍራንሲስኮ ቬራ ኮሎምቢያዊ ነው። የአካባቢ ጥበቃ እና የሕጻናት መብት ተሟጋች ነው።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት የተሻለ የትምህርት አቅርቦት ያስፈልጋል በማለቱ የግድያ ዛቻ ደርሶበት ነበር። ለታዳጊው የመብት ተሟጋች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እውቅና ሰጥቷል።
መንግሥት በበይነ መረብ ለሚማሩ ታዳጊዎች የኢንተርኔት አቅርቦቱን ማሻሻል አለበት ማለቱን ተከትሎ ካልታወቀ የትዊተር ተጠቃሚ የግድያ ዛቻ ደርሶታል።
ፍራንሲስኮ በደቡብ አሜሪካ ውስጥ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ምስጋና የሚያቀርብ ደብዳቤ ከተመድ ደርሶታል።
ከዚህ ቀደም በደቡብ አሜሪካ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች ተገድለዋል።
የ11 ዓመቱ ታዳጊ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ፤ የሚተቹትን ሰዎች ቢቀበልም ዛቻና ማስፈራሪያ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጿል።
ታዳጊው ላይ የግድያ ዛቻ መሰንዘሩ ብዙዎችን አስቆጥቷል።
ኮሎምቢያ ውስጥ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና በአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ተባብሷል።
"ኮሎምቢያ ውስጥ እንዲህ ያለ ዛቻ የተለመደ ነው። ተጠያቂ የሚደረግ አካል ግን የለም" የምትለው ሎርደስ ካስትሮ ናት።
ሎርደስ የምትሠራው የማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለሚመዘግብ ቡድን ነው።
"የ11 ዓመት ልጅ ላይ ማስፈራሪያ መሰንዘሩ ምን ያህል እንደዘቀጥን ያሳያል። የንግግር ነጻነት እንደማይከበርም ይጠቁማል" ትላለች።
የተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሚሼል ባችሌት ፊርማቸውን ያኖሩበት ደብዳቤ፤ ፍራንሴስኮን ያመሰግናል።
ዓለም እንደሱ አይነት ታዳጊ የመብት ተሟጋቾች እንደሚያስፈልጓትም ያትታል።

የፎቶው ባለመብት, DIANA LOSADA
"ለታዳጊዎች ሲባል የኢንተርኔት አገልግሎት መሻሻል እንዳለበትም እንስማማለን" ይላል ደብዳቤው።
ፍራንሲስኮ ከተመድ በተላከለት ደብዳቤ ደስተኛ እንደሆና የእድሜ እኩዮቹ ከሆኑ የመብት ተሟጋቾች ጋር መሥራት መቀጠል እንደሚፈልግ ተናግሯል።
ኮሎምቢያ ውስጥ ከተጀመሩ ንቅናቄዎች መካከል አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ፕላስቲክ እንዲታገድ የሚጠይቀው በዋነኛነት ይጠቀሳል።
ታዳጊው ስለ አካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረው በስድስት ዓመቱ ነው። ከቤተሰቦቹ ጋር በመሆን በሬ ማታገል (ቡልፋይቲንግ) እንዲቆም የተቃውሞ ሰልፍ ያካሂድ ነበር።
ለተፈጥሮ ያለው ፍቅር ወደ መብት ተቆርቋሪነት እንዳመራው ይናገራል።
ቁሳቁሶችን በድጋሚ ጥቅም ላይ ማዋል ያዘወትራል። በተከለሉ የተፈጥሮ አካባቢዎች የማዕድን ቁፋሮን ይቃወማል።
"ያደግኩት በተራራማ አካባቢ ከዳክዬዎች፣ ዶሮዎችና አእዋፍት ጋር ነው። የእንስሳት መብትና የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች የሆንኩት ለዚህ ነው" ይላል።
እአአ በ2019 በትውልድ ቀዬው ቪሌታ ውስጥ ጋርዲያንስ ኦፍ ላይፍ የተባለ የአካባቢ ጥበቃ ቡድን መስርቷል።
እሱና ስድስት የትምህርት ቤት ጓደኞቹ በጎዳናዎች ላይ ቆሻሻ እያነሱ ወደ ከተማ ማዕከል በማቅናት ሰልፍ ያካሂዳሉ።
ቡድኑ አሁን ላይ በ11 የአገሪቱ ግዛቶች 200 አባላት አሉት። ከኮሎምቢያ በተጨማሪ ከሜክሲኮና አርጀንቲናም ታዳጊዎች ቡድኑን ተቀላቅለዋል።
ፍራንሲስኮ በግሬታ ተንበርግ የተመሰረተው ፍራይዴይስ ፎር ፊውቸር ሙቭመንት አባል ነው።
"ታዳጊዎች ስለትልልቅ ርዕሰ ጉዳዮች ያላቸው አስተያየት ሊደመጥ ይገባል። ይህም የአየር ንብረት ለውጥና የምጣኔ ሀብት ፖሊሲን ይጨምራል። እኛ የወደፊት ዓለም ተረካቢዎች ብቻ አይደለንም። አዋቂዎች የሚወስኑት ውሳኔ ዛሬ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረብን ነው" ይላል።
እናቱ ማሪያ ማንዛሬዝ ልጇ ላይ የተሰነዘረው የግድያ ዛቻ ከማስፈራሪያ ያለፈ እንደማይሆን ተስፋ ታደርጋለች።
የመንግሥት ባለሥልጣኖች ጉዳዩን እንደሚመረምሩና ድጋፍ እንደሚያደርጉላት ነግረዋታል።
ከዚህ በፊት በልጇ የተሳለቁ ሰዎች ቢኖሩም የግድያ ዛቻ አልደረሰበትም ነበር።
"በጣም ከባድ ነገር ነው። ሆኖም ልጄ የተፈጠረውን ረስቶ የሚወደውን ነገር ማድረግ ላይ እንደሚያተኩር ባለ ሙሉ እምነት ነኝ" ብላለች።
ባለፈው ሳምንት የኮሎምቢያ ፕሬዘዳንት ኢቫን ዱኬ፤ ታዳጊውን ለመግደል የዛቱትን ሰዎች "ወንበዴ" ብለዋል። ፖሊስ ምርመራ መጀመሩንም አስታውቋል።
የተመድ አሐዝ እንደሚያሳየው፤ አምና ብቻ ኮሎምቢያ ውስጥ 53 የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ተገድለዋል። በተጨማሪም የ80 ማኅበረሰብ መሪዎች ግድያ ጉዳይ እየተጣራ ይገኛል።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ግሎባል ዊትነስ እንደሚለው በ2019 ኮሎምቢያ ውስጥ 64 የአካባቢ ጥበቃ ተቋርቋሪዎች ተገድለዋል።
ይህም በ2019 ለአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች አደገኛ በሆኑ አገሮች ዝርዝር ኮሎምቢያን ቀዳሚ አድርጓታል።












