ኮሚሽኑ በጋምቤላ ባደረገው ቅኝት ከ14 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ታስረው አገኘሁ አለ

አርማ
ታትሟል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጋምቤላ ክልል የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ አስቸኳይ ትኩረትን ይሻል አለ።

ኮሚሽኑ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በክልሉ የታሳሪዎች አያያዝ ሊሻሻል ይገባል እንዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲዎች በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት ሊከበር ይገባል ብሏል።

የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጋምቤላ ክልል አኝዋ ዞን ከታኅሣሥ 12 እስከ 15 2013 ተጉዞ እንደነበረ ገልጾ፤ በጎበኛቸው የክልሉ ማረሚያ ቤቶች በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች አያያዝና ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ሁኔታ በአፋጣኝ ሊሻሻል የሚገባው ነው ብሏል።

ኮሚሽኑ በክልሉ በነበረው ቆይታ የኦነግ ሸኔ አባላት ናቸው ተብለው ተጠርጥረው በእስር ላይ ያሉ የ11 እና 12 ዓመት ወንዶች እንዲሁም የ14 ዓመት ታዳጊ ሴት መመልከቱ እጅጉን እንዳሳሰበው በመግለጫው አትቷል።

ኮሚሽኑ ታዳጊ ወንዶቹ በእስር ላይ ሳሉ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው የገለጸ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙት ታዳጊዎች በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ እና የደረሰባቸው ጥቃት ምርመራ እንዲደረግ የክልሉን አስተዳዳሪዎች መጠየቁን በመግለጫው ገልጿል።

ኮሚሽኑ ጨምሮም የትግራይ ተወላጆች የሆኑ እና ለህወሓት ድጋፍ በማድረግ ተጠርጥረው የታሰሩ 90 እስረኞችን በሁለት እስር ቤቶች ውስጥ ማግኘቱን አስታውቋል።

ግለሰቦቹ ከኅዳር 5 ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኙ ጠቅሶ በእስረኞቹ ላይ እስካሁን ድረስ የምርመራ ሥራ አለመጀመሩን አስታውቋል።

በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎች የዋስትና መብታቸው እንዲከበር እና ፖሊስም በአስቸኳይ የወንጀል ምርመራውን እንዲጀምር የአከባቢው አስተዳዳሪዎችን መጠየቁን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በኦነግ ሸኔ አባልነት ተጠርጥረው የተያዙትን ታዳጊዎች ጨምሮ ለህወሓት ድጋፍ አድርጋችኋል ተብለው የታሰሩት ግለሰቦች በእስር ላይ ይገኛሉ ብሏል ኢሰመኮ።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) "የጋምቤላ ክልል መንግስት ትኩረትን የሚሹ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸው የሚታወቅ ቢሆንም፣ የሕፃናት እስረኞችና የተጠርጣሪ ታሳሪዎችን የዋስትና መብት ማረጋገጥ እጅግ አፋጣኝ ትኩረት ይሻል" ብለዋል።

ኮሚሽኑ በክልሉ በነበረው ቆይታ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ማነጋገሩን ገልጿል።

በዚህም መሠረት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምንም እንኳ የምርጫ ሥነ-ምግባር መግባቢያ ሰነድ" ቢፈርሙም፤ ቢሮና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ለማግኘት፣ በክልሉ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ለመስራትና፣ የፓርቲያቸውን ዝግጅቶችን ለማድረግ እንግልት እንደሚገጥማቸውና በአንዳንድ አባላቶቻቸው ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ እንዲሁም እስር መድረሱን ገልጸዋል ብሏል።

ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) "ሀገራዊ ምርጫው እየተቃረበ በመሆኑ፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የክልሉ እና የፌዴራል መንግስት አካላት የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸውን እንዲያረጋግጡ ያስፈልጋል" ብለዋል።