በሩስያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በምዕራብ ሩስያ የተቃውሞ ሰልፎች መካሄድ መጀመራቸውን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታሰሩ።
ዝነኛው ተቃዋሚ አሌክሲ ናቫልኒ መታሰሩን በመቃወም ሰልፍ ሲካሄድ ፖሊሶች ለመበተን ሞክረዋል። ካባሮቭስክ በተባለችው ግዛት ሰዎች ከቤት እንዳይወጡ ቢከለከልም ሰልፎች እየተካሄዱ ነው።
የናቫልኒ የቅርብ አጋሮች፣ ቃል አቀባዩና ከጠበቆቹ አንዱ በፖሊስ መታሰራቸው አይዘነጋም።
ናቫንሊም ባለፈው ሳምንት ከጀርመን ወደ ሩስያ ካቀና በኋላ በቁጥጥር ስር ውሏል።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የናቫንሊ ደጋፊዎች የጠሩት ሰልፍ በ60 የሩስያ ከተሞች ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
አንድ ገለልተኛ ምንጭ እንዳለው ቭላዲቮስቶክ በተባለ ግዛት ቢያንስ 3,000 ሰዎች ሰልፍ ወጥተዋል። የአገሪቱ ባለሥልጣኖች ግን ቁጥሩ 500 ነው ብለዋል።
አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል ፖሊሶች ተቃዋሚዎችን ሲያባርሩ ያሳያል።
በሩስያዋ ሰርቢያ ከተማ ቅዝቃዜው ከ50 ሴንቲ ግሬድ በታች ቢሆንም ተቃዋሚዎች ብርዱን ተቋቁመው ድምጻቸውን ለማሰማት ወስነዋል።
ገለልተኛ የተራድኦ ድርጅት እንደሚለው እስካሁን 48 ሰዎች ታስረዋል።
ሩስያ ሕገ-ወጥ ያለችውን ሰልፍ ለማፈን ጥብቅ ገደብ እንደምትጥል ባለሥልጣኖች አስታውቀዋል።
ተቃውሞ ይካሄድባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ቦታዎች አንዱ የሞስኮው ፑሽኪን አደባባይ ሲሆን፤ ፖሊሶች አከባቢውን በተጠንቀቅ እየጠበቁ ይገኛሉ።
ከጀርመን ወደ ሩስያ ከናቫንሊ ጋር ያቀናችው ባለቤቱ ዩሊያ በሞስኮው ሰልፍ እንደምትገኝ ተናግራለች።
"ለኔም፣ ለባለቤቴም፣ ለልጆቻችንና ለምናምንበት ነገር ስልም ሰልፉን እቀላቀላለሁ" ብላለች ዩሊያ።
በተለይም በወጣቶች ዘንድ ተወዳጅ የሆነው ቲክቶክ ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ሲጠራ ነበር።
ሰልፉ የተጠራው ናቫልኒ ከታሰረ በኋላ የተለቀቀ የምርመራ ቪድዮ፤ ፑቲን በሕገ ወጥ መንገድ ቅንጡ ቤተ መንግሥት ማስገንባታቸውን ካጋለጠ በኋላ ነው።
ቪድዮውን ከ65 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አይተውታል። ክሬምሊን በበኩሉ ፑቲን ቤተ መንግሥት አላስገነቡም ብሏል።
የምርመራ ቪድዮው እንደሚያሳየው፤ ቤተ መንግሥቱ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር ወጥቶበታል። "በታሪክ ትልቁ ጉቦ ነው" በማለት በቪድዮው ተገልጿል።
በደቡብ ሩስያ ብላክ ሲ አካባቢ የሚገኘው ቤተ መንግሥት የሞኖኮ 39 እጥፍ ስፋት እንዳለው ተገልጿል።
የምርመራ ቪድዮው እንደሚያሳየው ቤተ መንግሥቱ የተሠራው በፑቲን የቅርብ ሰዎች ሕገ ወጥ የገንዘብ ድጋፍ ነው። የነዳጅ ምርት ባለሥልጣኖች እና ቢሊየነሮች ከነዚህ መካከል ናቸውም ተብሏል።
ናቫንሊ በጸረ ሙስና ንቅናቄው ይታወቃል። እአአ 2018 ላይ ፑቲን ተቀናቃኝ ሆኖ ምርጫ ሊወዳደር ሲል ገንዘብ የመበዝበዝ ክስ ተመስርቶበታል።
ታዋቂው ሩስያዊ ተቃዋሚ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች አሉት።
የ44 ዓመቱ ተቃዋሚ ባለፈው ነሐሴ ተመርዞ ለሞት ተቃርቦ ነበር። ለመመረዙ ተጠያቂው ፑቲን እንደሆኑ ቢናገርም፤ የሩስያ መንግሥት እጁ እንደሌለበት አስታውቋል።
ናቫንሊ ከተመረዘ በኋላ ጀርመን ውስጥ ህክምና ሲከታተል ነበር። ወደ ሩስያ ከተመለሰ እንደሚታሰር ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም ወደ አገሩ ከመመለስ ወደኋላ አላለም።
የቀረበበትን ክስ "ፍትሕ ላይ መቀለድ ነው። ሕገ ወጥነት መንሰራፋቱን ያሳያል" ሲል ተችቷል።












