የተቃውሞ ሰልፍ በተጠራባት ሩስያ የናቫልኒ ረዳቶች ታሰሩ

የሩስያ ፖሊስ የአሌክሲ ናቫልኒ የቅርብ ረዳቶችን እያሰረ ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

የሩስያ ፖሊስ የአሌክሲ ናቫልኒ የቅርብ ረዳቶችን እያሰረ ነው።

ታዋቂው ሩስያዊ ተቃዋሚ ናቫልኒ እስር ላይ ሲሆን፤ ደጋፊዎቹ ነገ የተቃውሞ ሰልፍ እንዲካሄድ በማኅበራዊ ሚዲያ እየቀሰቀሱ ነው።

የሞስኮ ፖሊስ እነዚህ የተቃውሞ ሰልፎች ፍቃድ አልተሰጣቸውም ብሏል።

ናቫልኒ ከታሰረ በኋላ የተለቀቀ የምርመራ ቪድዮ፤ ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሕገ ወጥ ገንዘብ ቅንጡ ቤተ መንግሥት እንዳስገነቡ ያጋልጣል።

ቪድዮውን ከ55 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አይተውታል። ክሬምሊን በበኩሉ ፑቲን ቤተ መንግሥት አላስገነቡም ብሏል።

ናቫልኒ ከጀርመን ወደ ሩስያ ካቀና በኋላ ነበር በቁጥጥር ስር የዋለው።

ነሐሴ ላይ ተመርዞ ለሞት ተቃርቦ እንደነበር ይታወሳል። ናቫንሊ ከተመረዘ በኋላ ጀርመን ውስጥ ህክምና ሲከታተል ነበር።

ወደ ሩስያ ከተመለሰ እንደሚታሰር ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም ወደ አገሩ ከመመለስ ወደኋላ አላለም።

ናቫልኒ በቅድመ ምርመራ ለ30 ቀናት የታሰረ ሲሆን፤ ገንዘብ በመበዝበር የቀረበበትን ክስ በመጣሱ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል። እሱ ግን እስሩ ፖለቲካዊ ነው ይላል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የቅርብ ረዳቶቹ መካከል ቃል አቀባዩ ኪራ ያርመይሽና ከጠበቆቹ አንዱ ሊቦቭ ሶቤል ይገኙበታል።

በጸረ ሙስና እንቅስቃሴው የሚታወቀው ናቫልኒ፤ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሉት ሲሆን፤ የፑቲንን አስተዳደር "ፊውዳል" እና "በቀማኞች የተሞላ" ሲል ይተቻል።

ናቫንሊ የለቀቀው የምርመራ ቪድዮ እንደሚያሳየው ቤተ መንግሥቱ የተሠራው በፑቲን የቅርብ ሰዎች ሕገ ወጥ የገንዘብ ድጋፍ ነው። የነዳጅ ምርት ባለሥልጣኖች እና ቢሊየነሮች ከነዚህ መካከል ናቸውም ተብሏል።

ናቫንሊ በቪድዮው "በዚህ ገንዘብ ለአለቃቸው ቤተ መንግሥት ሠርተዋል" ብሏል።

የሩስያ ብሔራዊ የምርመራ ተቋም ቤተ መንግሥቱ ዙርያ ያለው 27 ስኩዌር ማይል መሬት ባለቤት እንደሆነም በቪድዮው ተጠቁሟል።

ሕንጻው ውስጥ ካዚኖ (መቆመሪያ)፣ የበረዶ ሆኪ መጫወቻና ወይን ማቀነባበሪያ ይገኛል ተብሏል።

"ለመጣስ የሚከብድ አጥር አለው። ራሱን የቻለ ወደብና ቤተ ክርስቲያን አለው። በረራ ማድረግ ክልክል ነው። የድንበር ላይ ጥበቃ ኃይልም አለው። ሩስያ ውስጥ ያለ ራሱን የቻለ አገር ነው" ሲል ናቫንሊ ተናግሯል።

የናቫንሊ ደጋፊዎች የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድ ቢያቅዱም የአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ ከልክሏል። የሩስያ የትምህርት ሚንስትር ወላጆች ልጆቻቸው በተቃውሞው እንዳይሳተፉ እንዲከለክሉ አሳስቧል።

በሌላ በኩል በጥበብ ዘርፍና በስፓርት ታዋቂ የሆኑ ሩስያውያን ለናቫልኒ ድጋፍ አሳይተዋል።

ነገ የተቃውሞ ሰልፍ እንዲካሄድ ጥሪ ከተላለፈባቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች መካከል ቲክቶክ በዋነኛነት ይጠቀሳል።

ሳልቫ ቫርፎሎሜቭ የተባለ ታዋቂ ሩስያዊ የቲክቶክ ተጠቃሚ "ቲክቶክ ላይ የሚታየው ቪድዮ ስለ ፑቲን ቅንጡ ቤተ መንግሥትና የናቫልኒ መታሰር ሆኗል" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።