ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እግር ኳስ ፡ የልምምድ ቦታ ክስተቶች ማፈትለካቸው አሰልጣኝ ማይክል አርቴታን አስቆጣ
የአርሰናሉ አሰልጣኝ ማይክል አርቴታ በዳኒ ሴባዮስ እና በዴቪድ ሉዊዝ መካከል የተፈጠረውን ችግር ይፋ ያደረጉ አካላት የእጃቸውን ያገኛሉ ሲሉ ገለጹ።
በልምምድ ወቅት ሴባዮስ አደገኛ አጨዋወት መምረጡን ተከትሎ ሁለቱ ተጫዋቾች ተጋጭተው ሉዊዝ በሰነዘረው ቡጢ የቡድን አጋሩ መድማቱን ሪፖርቶች ገልጸዋል፡፡
አርቴታ ድርጊቱን "ምንም አይደለም" ሲሉ የገለጹ ሲሆን ከዚያ ይልቅ ጉዳዩ ይፋ መሆኑ ይበልጥ እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል፡፡
"እኔ ክስተቱ መውጣቱን በጭራሽ አልወደድኩትም" ብለዋል፡፡
ስፔናዊው አሰልጣኝ አክለውም "ከየት እንደመጣ ማወቅ እፈልጋለሁ። እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ከሌላው የምጠብቀውን ግላዊ እና ሚስጥራዊ ነገሮችን መያዝን ሙሉ በሙሉ የሚፃረር ስለሆነ መዘዞች ይኖራሉ" ብለዋል፡፡
ክስተቱን እንዲያብራሩ የተጠየቁት አርቴታ ፣ "ልምምዶች በጣም ፉክክር ያለባቸው ናቸው። እነዚህ ጉዳዮች ብዙ ጊዜ የሚከሰቱ ናቸው። ሲከሰቱም በቡድኑ ወዲያውኑ መፍትሄ ያገኛሉ። ስለዚህ ብዙም የምለው ነገር የለም" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
"በጭራሽ ምንም ችግር የለም " ሲሉም አክለዋል፡፡
ከሪያል ማድሪድ በውሰት ለአርሴናል በመጫወት ላይ ሚገኘው የስፔኑ አማካይ ሴባዮስ መረጃው ሐሙስ ይፋ ከሆነ በኋላ በማህበራዊ ሚዲያው ዘገባውን ውድቅ አድርጎታል፡፡
የ 24 አመቱ ተጫዋች ከመድፈኞቹ ተጫዋቾች ጋር በአደባባይ አለመግባባት ሲፈጠር የመጀመሪያው አይደለም፡፡
አርሰናል ፉልሃምን 3-0 ባሸነፈበት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ተቀይረው ለመግባት ሲያሟሙቁ ከኤዲ ንኬቲያ ጋር መጋጨታቸው ይታወሳል፡፡
የ 33 ዓመቱ ብራዚላዊው ሉዊዝ በ2019 ነበር ቼልሲን ለቅቆ አርሰናልን የተቀላቀለው፡፡