ሩሲያ ፡ ቭላድሚር ፑቲንና ቤተሰባቸው ሕይወታቸውን ሙሉ ላይከሰሱ ነው

ቭላድሚር ፑቲንና ቤተሰባቸው ሕይወታቸውን ሙሉ ላይከሰሱ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

የሩሲያ ፓርላማ የታችኛው ምክር ቤት (ዱማ) ለቭላድሚር ፑቲንና ቤተሰባቸው የሕይወት ዘመን ያለመከሰስ መብትን ሊያጎናጽፋቸው ነው።

ይህ ውይይት እየተደረገበት ያለው ረቂቅ ሕግ ፑቲንም ሆኑ ቤተሰባቸው ሥልጣን ከለቀቁ በኋላ አንድም አካል ክስ ሊመሰርትባቸው አይችልም፤ በሕግም ተጠያቂ አይሆኑም፤ ይህም እስከ ሕይወት ዘመናቸው ማብቂያ የሚዘልቅ ነው።

ይህ ረቂቅ ባለፈው ሐምሌ ሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ከተወሰኑ አንቀጾች አንዱ ነው።

በሩሲያ የታችኛውም ሆነ የላይኛው ምክር ቤት በፑቲን ደጋፊዎች የተሞላ ነው።

የቭላድሚር ፑቲን 4ኛ የሥልጣን ዘመን ከሦስት ዓመት በኋላ በፈረንጆቹ 2024 ይጠናቀቃል።

ሆኖም ከዚያ በኋላ ለሌላ 8 ዓመታት በሥልጣን እንዲቆዩ ከወዲሁ ተፈቅዶላቸዋል። ይህም ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያን እስከ 2032 ዓ/ም ከክሬምሊን አይወጡም ማለት ነው።

ቭላድሚር ፑቲን አሁን 68 ዓመታቸው ነው። ተተኪም አላዘጋጁም። በቅርብ ጊዜ ወዲህም በጤናቸው ዙርያ ያልተረጋገጡ ወሬዎች ሲወጡ ነበር።

ፑቲን ክሬምሊን የገቡትና ሩሲያን መምራት የጀመሩት በፈረንጆቹ ከ2000 ዓ/ም ጀምሮ ነው።

ቭላድሚር ፑቲን ይህ የሕይወት ዘመን ያለመከሰስ መብት ለምን አስፈለጋቸው የሚለው ጉዳይ በሰውየው የወደፊት የፖለቲካ ሕይወት ላይ አዲስ ጥርጣሬን ፈጥሯል።

ገና 8 ዓመታት በክሬምሊን የሚቆዩ ከሆን ይህን ሕግ ከወዲሁ እንዲጽደቅ ለምን ቸኮሉ የሚለውም ለፖለቲካዊ መላምቶች በር ከፍቷል።

የፑቲን ቀንደኛው ተቺና ተመርዞ በከፍተኛ ርብርብ በሕይወት መትረፍ የቻለው አሌክሲ ናቫልኒ በትዊተር ሰሌዳው "ፑቲን የሕይወት ዘመን ያለመከሰስ መብት ሕግ አሁን ለምን አስፈለገው? አምባገነንስ በራሱ ፈቃድ ሥልጣን ሊለቅ ይችላልን?" ሲል ጠይቋል።

ይህ ረቂቅ በታችኛው ፓርላማ ማክሰኞ የመጀመርያ ዙር ድምጽ ሲሰጥበት 37 የምክር ቤት አባላት ብቻ ናቸው ረቂቁን የተቃወሙት።

ረቂቁ ከዚህ በኋላ በዱማው ውስጥ ድጋሚ ክርክር ተደርጎበት 2 ጊዜ ድምጽ ይሰጥበታል።

ከዚያ የፌዴሬሽን ካውንስል የሚባለው የላይኛው ምክር የመጨረሻ ድምጽ ከሰጠበት በኃላ ፑቲን ራሳቸው ፊርማቸውን አኑረው ሕግ ያደርጉታል።

ይህ ረቂቅ ሕግ ሆኖ ሲጸድቅ ፑቲንም ሆኑ ቤተሰባቸው ዕድሜ ልካቸውን ለፈጸሙትም ሆነ ወደፊት ለሚፈጽሙት ማንኛውም ወንጀል በፖሊስ አይጠየቁም፣ ምርመራም አይደረግባቸውም፣ ያፈሩትን ንብረትም አይወረስም፣ ቤታቸውም አይበረበርም።

በአጠቃላይ በሕይወት ዘመናቸው ለሰሩት ማንኛውም ጥፋት ተጠያቂ አይሆኑም። በረቂቁ መሰረት ብቸኛው ተጠያቂ የሚያደርጋቸው ወንጀል አገር ከከዱ ብቻ ነው።

በአሁኑ ሰዓት በሩሲያ የቀድሞ የሩሲያ ፕሬዝዳንት የነበሩና እስከዛሬም በሕይወት ያሉት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ብቻ ናቸው።