1ሺ 600 አፍሪካዊ ስደተኞች በጀልባ ስፔን ገቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በርካታ ቁጥር ያላቸው አፍሪካዊያን ስደተኞች በታንኳ አቆራርጠው ስፔን ካናሪ ደሴት ገብተዋል።
የስፔን የአስቸኳይ እርዳታ ሰጪዎች እንደተናገሩት 1ሺህ የሚሆኑት ስደተኞች ወደ ደሴቲቱ የገቡት ቅዳሜ ዕለት ነው።
እነዚህም በ20 ጀልባዎች ላይ ተፋፍገው ተጭነው ነው በሕይወት መድረስ የቻሉት።
አንድ ሰው ወዲያውኑ በሄሌኮፍተር ወደ ሆስፒታል ተወስዷል፥ በአሳሳቢ ሁኔታ ይገኝ ስለነበረ።
ከቅርብ ወራት ወዲህ ካናሪ አይላንድ ለመግባት የሚጣጣሩ በርካታ የምዕራብ አፍሪካ ተወላጆች በስፋት ተስተውለዋል። ከዚህ ቀደም የጉዞ መስመራቸው ጣሊያን ሲሆን በስፔን በኩል ወደ አውሮጳ ለመግባት ብዙም አልተለመደም ነበር።
ካናሪ ደሴት ከሰሜን አፍሪካ ጠረፍ የ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ብቻ ነው ያለው።
የስፔን ባለሥልጣናት እንደሚሉት ከሆነ በዚህ ዓመት ብቻ 11ሺ አፍሪካዊያን ወደ ካናሪ ደሴት ገብተዋል። ባለፈው ዓመት ወደ ደሴቲቱ መግባት የቻሉት ግን 2ሺህ 557 ብቻ ነበሩ።
በጀልባ ጉዞዎቹ ታዲያ ሁሉም ስደተኞች በሕይወት ይደርሳሉ ማለት አይደለም። በርካታ ጊዜያት ሬሳቸው ባሕር ላይ የሚቀሩ ብዙ አፍሪካዊያን አሉ።
ለምሳሌ በዚህ ዓመት ብቻ 414 አፍሪካዊያን በዚህ አቋራጭ መንገድ በጀልባ ስፔን ካናሪ ደሴት ለመግባት ሲሞክሩ ሞተዋል።
ይህ አሐዝ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ነው ይፋ ያደረገው።












