ተወዳጁ የጥያቄና መልስ ውድድር አቅራቢ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

ታትሟል

ተወዳጁ የጥያቄና መልስ ውድድር አቅራቢ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ተከትሎ ዓለም ሐዘኑን እየገለጸ ነው።

አሌክስ ትሬቤክ አሜሪካዊ የቴሌቪዥን ጥያቄና መልስ አሰናጅ ነበር። ብዙ ኢትዮጵያዊያን "ጀፐረዲ" በተሰኘው የቴሌቪዥን ጥያቄና መልስ ትእይንቱ ያውቁታል። ምክንያቱም ይህ ትእይንት በሳተላይት በነጻ ከሚደርሱ ፕሮግራሞች መሀል አንዱ ነበረና።

የጀፐረዲ ጥያቄና መልስ አሰናጅ ተወዳጁ አሌክስ ትናንት በተወለደ በ80 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

አሌክስ ትሬቤክ ደረጃ4 የጣፊያ ካንሰር ታማሚ እንደሆነ ይፋ ያደረገው ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ነበር።

አሌክስ "ጂፐረዲ" የተሰኘውን እጅግ ተወዳጅ የጥያቄና መልስ የቴሌቪዥን ትእይንት ማቅረብ የጀመረው ከፈረንጆቹ 1984 ዓ.ም ጀምሮ ነው።

በተወዳጅ አቀራረቡም በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ማሸነፍ ችሏል።

ሶኒ ፒክቸርስ ስለ ባወጣው የሐዘን መግለጫ "37 ዓመታትን ለቤተሰቦች ድምቀት የነበረ፣ ድምጹ ለሚሊዮኖች ምቾት የሰጠ" ሲል አሞካሽቶታል።

አሌክስ በጥያቄና መልስ ትእይንቱ መሀል ጣል ያደርጋቸው የነበሩ ቀልዶች ይበልጥ ተወዳጅ አድርገውታል።

ካናዳዊ አሜሪካዊው አሌክስ ትሬቤክ 8ሺህ 200 የጥያቄና መልስ ትእይንቶችን ለ37 ዓመታት መርቷል።

በዚህም የተነሳ በካናዳና አሜሪካ በተለየ እጅግ እውቁ የቴሌቪዥን አቅራቢ ለመሆን በቅቷል። ሆኖም የርሱ ዝና በሰሜን አሜሪካ ብቻ የሚወሰን አይደለም። እንደዛሬው በርካታ የቴሌቪዥን ትእይንቶች ባልነበሩበት ዘመን አሌክስ ለሚሊዯን የዓለም ሕዝቦች በቴሌቪዥናቸው መስኮት ብቅ እያለ አዝናንቷቸዋል።

በ2014 የጊነስ የዓለም ክብረወሰኖች መዝገብ "አንድን ትእይንት ወይም ውድድር ለረዥም ጊዜ አሰናጅ ሆኖ በማቅረብ የመጀመርያ ሰው" በሚል እውቅና ሰጥቶታል።

አሌክስ የካንሰር ሕመምተኛ ሆኖ ሳለ ትእይንቱን ለመምራት ወስኖ ነበር።

ለካንሰሩ ኪሞቴራፒ ሕክምና በመውሰድ ላይ ሳለ የፈረመው ኮንትራት እስከ 2022 ዓ.ም. ትእይንቱን እንዲመራ ስለሚያስገድደው ይህንኑ ውል ታማኝ ሆኖ ለመጨረስ ጥረት አድርጎ አልተሳካለትም።

በአሌክስ ሞት በዓለም ዙርያ በርካታ ሰዎች ሐዘናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

የካናዳው ፕሬዝዳንት ጀስቲን ትሩዶ "የሚሊዮኖችን ቤተሰብ ያደመቀ ደማቁ ካናዳዊ አረፈ" ሲሉ መሪር ሐዘናቸውን ገልጠዋል።