የሕንዱ አየር መንድ ባህር ላይ የሚያርፉ አውሮፕላኖች መጠቀም ሊጀምር ነው

ሕንድ ባህር ላይ የሚያርፉ አውሮፕላኖች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የሕንዱ ስፓይስጀት አየር መንገድ ከባህር የሚነሱና ባህር ላይ ማረፍ የሚችሉ (ሲፕሌንስ) አውሮፕላኖችን መጠቀም ሊጀምር ነው።

ወረርሽኙ ተጽዕኖ ያሳደረበት የበረራው ዘርፍ እንዲያገግም ይረዳልም ተብሏል።

የአገሪቱ ትልቁ አየር መንገድ 18 የባህር አውሮፕላኖች ለማብረር ፍቃድ አለው።

ከጉዞ መዳረሻዎቹ አንዱ የዓለም ትልቁ ሀውልት የሚገኝበት ኬቫዲያ ግዛት ነው።

ስፓይሰጀት አየር መንገድ በኮቪድ-19 ሳቢያ አማራጭ የገቢ ምንጮችን እየፈለገ ነው። ካርጎ ማመላለስ እና ከግዛት ወደ ግዛት በትንንሽ አውሮፕላኖች በረራ ማካሄድ ከስልቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ።

በመላው ዓለም ያሉ አየር መንገዶች በወረርሽኙ ሳቢያ ገቢያቸው ተቃውሷል። ብዙዎቹ ሠራተኛ ለመቀነስም ተገደዋል።

አንዳንድ አየር መንገዶች ምግብ ማመላለስን እንደ አማራጭ የገቢ ምንጭ ወስደዋል።

የስፓይስጀት ኃላፊ አጄ ሲንግ እንዳሉት፤ ከባህር የሚነሱና ባህር ላይ ማረፍ የሚችሉ (ሲፕሌንስ) አውሮፕላኖች አንዱን ግዛት ከሌላው ያስተሳስራሉ።

"አውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት ከፍተኛ ወጪ ሳይወጣ ግዛቶችን ማገናኘት ይቻላል" ብለዋል።

የሕንድ ጠቅላይ ሚንስትር ንሬንድራ ሞዲ፤ ቅዳሜ ከአሕመድባድ ወደ ኬቫዲያ የሚደረገው የመጀመሪያ በረራ ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እለቱ በኬቫዲያ የመታሰቢያ ሀውልት የተሠራላቸው ቫልቢሀቢ ፓታል 145ኛ ዓመት ክብረ በዓል ነው።

በረራው 30 ደቂቃ የሚወስድ ሲሆን፤ ለአንድ ነጠላ ጉዞ 1500 ሩፒ ወይም ወደ 20 ዶላር ገደማ ይጠየቅበታል።

ለበረራ የሚውለው ትዊን ኦተር 300 አውሮፕላን የሚሠራው በቫይኪንግ ኤር ነው። አብራሪና አስተናጋጆችን ጨምሮ 19 ተሳፋሪዎች ይጭናል።

አነስተኛ መጠን ያለው በመሆኑ ግዙፍ አውሮፕላኖች መድረስ የማይችሉበት ቦታ ጥቅም ላይ ይውላል።