በሆላንድ የኤርትራ ቆንሱላ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ታገዱ

ታትሟል

የሆላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሄግ የሚገኘውን የኤርትራ ቆንሱላ ፅህፈት ቤት ኃላፊን አገደ።

እግዱም የተላለፈው ቆንሱላው "ህጋዊ ባልሆነ መንገድ" ውጭ ከሚኖሩ ኤርትራውያን ገንዘብ እየሰበሰበ ነው የሚል ክስ ከቀረበበት በኋላ መሆኑንም የሆላንድ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

ኤምባሲው "በማስፈራራትና በማስገደድ ጭምር በውጭ ያሉ ኤርትራውያን የዲያስፖራ ግብር እንዲከፍሉ ያስገድድ" እንደነበርና ከዚህ ተግባሩ እንዲቆጠብ በተደጋጋሚም ተገልፆለት እንደነበር የሆላንድ መንግሥት ባወጣው መግለጫ አትቷል።

በዚህም ምክንያት "ይህንን ያልተለመደ እርምጃ ለመውሰድ እንደተገደደም" ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪ የሆላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስቴፍ ብሎክ በብራስልስ የሚገኙትን የኤርትራ አምባሳደርም ክፍያዎች እንዲቆሙ ለማስጠንቀቅ ጠርተው አናግረዋቸው ነበር በማለት ኤንኦኤስ የተባለው የሆላንድ ሚዲያ ዘግቧል።

ከሁለት አመት በፊትም የኤርትራ ቆንሱላ በውጭ የሚኖሩ ኤርትራውያን ከገቢያቸው 2 በመቶ "የዲያስፖራ ግብር" እንዲከፍሉ ማስገደዱ ህጋዊነት የለውም በሚል እንዲወጣ ተገዶ ነበር።

ሆኖም የኤምባሲዎች አገልግሎት የሚፈልጉ አንዳንድ ኤርትራውያን ይህንን ክፍያ ለመክፈል መገደዳቸውን ይናገራሉ።

ክፍያው የተጣለው አገሪቷ ነፃነቷን ካገኘችበት ከጎሮጎሳውያኑ 1991 ጀምሮ ነው።

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በበኩሉ "ይህ ውንጀላ ነው" በማለት ያጣጣለው ሲሆን የሆላንድ መንግሥትንም የቆንሱላ ሰራተኞቹን ትንኮሳ እያደረሰባቸው ነው በማለት ወንጅሏል።

የተባለው ህጋዊ ያልሆነ የተጣለ ክፍያ የለምም ብሏል።

በዚህ ሳምንት ማክሰኞም የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገብረ መስቀል እግዱን አስመልክቶ "ተቀባይነት የሌለው ባህርይ ነው። ጠባብ የሆኑ ቡድኖችን ፍላጎት ለሟሟላት የተወጠነ ነው" ብለውታል

በሚቀጥሉት ቀናትም የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሱዳን ተቀማጭ የሆኑትንና በተጨማሪነት በኤርትራ የሚሰሩትን የሆላንድ አምባሳደር ጠርቶ በዚህ ተደጋጋሚና ተቀባይነት በሌለው ተግባር የተሰማውን ተቃውሞ እንደሚገልፅ አስታውቋል።

በቀጣይነትም ተገቢና ተመጣጣኝ እርምጃም ኤርትራ እንደምትወስድ ሚኒስቴሩ አፅንኦት ሰጥቷል።

ኤርትራ ምን አይነት እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ያልገለፀች ሲሆን ሆላንድ በአስመራ ኤምባሲ የላትም።

በሱዳን ተቀማጭ የሆኑት የሆላንዱ አምባሳደር ስለዚህ ጥሪ የደረሳቸው ነገር እንደሌለ ቢቢሲ ከምንጮቹ አረጋግጧል።

የኤርትራ መንግሥት በውጭ የሚገኙ ዜጎቹን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመዋጋት ያስችል ዘንድ ለብሄራዊ ፈንዱ የገንዘብ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ሲያበረታታ ነበር።

አንዳንዶችም መንግሥት ፈንዱን የሚያስተደድርበት መንገድ ግልፅነት የለውም በማለት ይተቻሉ።