ታንዛንያውያን መሪያቸውን እየመረጡ ነው

ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡት 29.1 ሚሊዮን ታንዛናዊያን እስከ ከሰዓት 10 ሰዓት ድረስ ድምጽ ይሰጣሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡት 29.1 ሚሊዮን ታንዛናዊያን እስከ ከሰዓት 10 ሰዓት ድረስ ድምጽ ይሰጣሉ።
ታትሟል

በታንዛንያው አገራዊ ምርጫ መራጮች ከንጋት ጀምሮ ድምጽ መስጠት ጀምረዋል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ መራጮች ድምጻቸውን እየሰጡ የሚገኙት በመላው አገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት ገደብ ተጥሎበት እና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለው በሚገኙበት ሁኔታ ውስጥ ነው።

ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡት 29.1 ሚሊዮን ታንዛናዊያን እስከ ከሰዓት 10 ሰዓት ድረስ ድምጽ ይሰጣሉ። አጠቃላይ የምርጫው ውጤት ደግሞ ከአንድ ሳምንት በኋላ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በአጠቃላይ 15 እጩዎች የታንዛኒያ ቀጣይ ፕሬዝደንት ለመሆን እየተወዳደሩ ይገኛሉ። ፕሬዝንዳንት ጆን ማጉፉሊ ግን ሰፊ የማሸነፍ ዕድል ተሰጥቷቸዋል።

የፕሬዝደንት ማጉፉሊ ፓርቲ የሆነው ቻማ ቻ ማፔንዱዚ እአአ ከ1961 የታንዛኒያ ነጻነት ወዲህ አገሪቱን ሲያስተዳድር ቆይቷል።

ፕሬዝደንት ማጉፉሊ ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን እየተወዳደሩ ይገኛሉ።

ዋነኛ ተቀናቃኛቸው ቱንዱ ሊሱ ናቸው። ተቃዋሚው ቱንዱ ከሶስት ዓመት በፊት ከግድያ ሙከራ አምልጠዋል። በግድያው ሙከራ ወቅት በጥይት የተመቱት ቱንዱ ለረጅም ጊዜ በቤልጄም አገር ሕክምና ሲከታተሉ ቆይተዋል።

ትዊተር ትናንት በታንዛኒያ የትዊተር አገልግሎቱን ለማቋረጥ ሙከራ እየተደረገ ነው ሲል አሳውቋል። ትዊተር ጨምሮ የታንዛኒያ መንግሥት "መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት መከበር አለበት" ብሏል።

ከትዊተር በተጨማሪም በርካታ የዋትስአፕ ተጠቃሚዎች ከመተግበሪያው ላይ ፎቶ እና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ማውረድ እንደተሳናቸው እየተናገሩ ይገኛሉ።

ትናንት ደግሞ የዛንዚባር ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪው በቁጥጥር ስር እንደዋለበት አስታውቋል። ማሊም ሰይፍ ትናንት በፖሊሶች መወሰደቻውን 'አክት ዋዛሌንዶ' ፓርቲ አስታውቋል።

በታንዛኒያ የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ራይት በምርጫው ዋዜማ በዛንዚባር እና መላው ታንዛኒያ እየተከሰቱ ያሉ እስር፣ ግድያዎችና አመጽ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

ዛንዚባር በታንዛኒያ ባህር ዳርቻዎች አካባቢ የሚገኙ የደሴቶች ስብስብ ስትሆን በከፊል ራስ ገዝ አስተዳደር ናት።

የዛንዚባር ነዋሪዎች መሪዎቻቸውን የሚመርጡ ሲሆን ይህ ደግሞ የዛንዚባርን ፕሬዝዳንትና በአጠቃላይ የታንዛኒያ አጠቃላይ ምርጫ ላይም እንዲሳተፉ ያደርጋቸዋል።