ፖሊስ ጥቁር አሜሪካዊን መግደሉን ተከትሎ በፊላዴልፊያ አዲስ አመጽ ተቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በፊላዴልፊያ ፖሊስ ጥቁር አሜሪካዊን መግደሉን ተከትሎ ለሁለተኛ ሌሊት በቀጠለው አለመረጋጋት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዘራፊዎች በከተማው የሚገኙ የንግድ ተቋማትን እየዘረፉ መሆኑን ፖሊስ ገለጸ።
አለመረጋጋቱን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የፖሊስ እና የብሔራዊ ጥበቃ አባላት ተሰማርተዋል። በመጀመሪያ ቀን ግጭት 30 ፖሊሶች ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል ባለሥልጣናት።
ፖሊስ የ27 ዓመቱን ዋልተር ዋላስ ላይ የተኩስ እሩምታ የከፈተው የያዘውን ቢላዋ እንዲወረውር የተሰጠውን ትዕዛዝ ችላ በማለቱ ነው ሲል ፖሊስ ገልጿል።
የዋላስ ቤተሰቦች በበኩላቸው ግለሰቡ የአዕምሮ ጤና ቀውስ እንደነበረበት ተናግረዋል።
ማክሰኞ ምሽት ፖሊስ ሰፋ ያለ ዝርፊያ ከተፈጸመባቸው አካባቢዎች ነዋሪዎች እንዲርቁ አስጠንቅቆ ነበር።
በከተማዋ ዙሪያ ያሉ ሱቆች ቀደም ብለው ተዘግተው ነበር።
ፋርማሲዎች በመዘጋታቸው ነዋሪዎች መድኃኒት ማግኘት እንዳልቻሉ የአሜሪካው የቢቢሲ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።
ዲሞክራቱ የከተማዋ ከንቲባ ጂም ኬኒ ፖሊስ የፈጸመው ግድያ "መመለስ ያለባቸው ከባድ ጥያቄዎች እንዳሉ የሚያሳይ ነው" ብለውታል።
የፊላዴልፊያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤሌ አውትላው ቦታውን እንደጎበኙ እና "የህብረተሰቡ ቁጣ" እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።
ተጨማሪ ሕዝባዊ አመጾች እንደሚኖሩ እና ለዚህም ተጨማሪ የፖሊስ ኃይል እንደሚያሠማሩ አስታውቀዋል።
በያዝነው የፈረንጆች ዓመት መጀመሪያ በሚኒሶታ ጆርጅ ፍሎይድ የተባለ ጥቁር አሜሪካዊ በፖሊስ መገደሉን ተከት በፊላደልፊያ ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።
ሰኞ ምሽት ከ 300 በላይ ሰዎች የዋላስን ግድያ በመቃወም ወደ አደባባይ የወጡ ሲሆን 91ቱ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከስፍራው የተገኙ ምስሎች የፖሊስ ተሽከርካሪ ሲቃጠል አሳይተዋል። በርካታ የንግድ ቤቶችና ሱቆችም ተዘርፈዋል።
ሰኞ ከሰዓት በምዕራብ ፊላዴልፊያ ኮብስ ክሪክ በሚባለው አካባቢ አንድ መሳሪያ የታጠቀ አንድ ሰው እንዳለ ሪፖርት መደረጉን ተከትሎ ሁለት አባላቱ ወደ ስፍራው ማቅናታቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ ታንያ ሊትል ለኤፒ የዜና ወኪል እንደገለፁት ዋላስ የተባለው ግለሰብ ቢላዋ ይዞ የነበረ ሲሆን እንዲጥል የቀረበለተን ትዕዛዝ ወደ ጎን በማለት "ወደ እነሱ ቀረበ" ብለዋል።
ሁለቱም የፖሊስ መኮንኖች በተደጋጋሚ በመተኮስ ዋላስን ትከሻቸው እና በደረቱ ላይ መትተዋል ብለዋል።
ከፖሊስ መኮንኖቹ አንዱ ዋላስን ወደ ሆስፒታል ቢወስዱም ህይወቱ እንዳለፈ ተናግሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዋላስ ቤተሰብ ጠበቃ የዋልተር ዋላስን የአዕምሮ ህመም እንዲረዳ ፖሊስን ሳይሆን አምቡላንስን እንደጠሩ ተናግረዋል።













