የአውሮፓ ዕለታዊ የኮቪድ ሞት ካለፈው ሳምንት አንጻር 40 በመቶ ከፍ ብሏል

አውሮፓ ኮቪድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በአውሮፓ በየቀኑ የሚመዘገበው የሞት መጠን ካለፈው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር በ40 በመቶ መጨመሩን የዓለም ጤና ድርጅት ለቢቢሲ ገለጸ።

የድርጅቱ ቃል አቀባይ ዶ/ር ማርጋሬት ሃሪስ እንደተናገሩት ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ እንግሊዝ፣ ኔዘርላንድስ እና ሩሲያ በአንድ ሦስተኛ ባደገው ቁጥር ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ይዘዋል።

"በሆስፒታሎች ውስጥ የጽኑ ህሙማን የህክምና ክፍሎች በጣም በታመሙ ሰዎች መሞላት ጀምረዋል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሩሲያ በቀን 320 የሆነ ከፍተኛ ሞት በማስመዝገብ በአጠቃላይ በቫይረሱ ህይወታቸው ያጡ ሰዎች ቁጥር ከ26ሺህ በላይ አድርሶታል።

ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በ 221 ሰዎች ሞት ምክንያት በጣሊያን ውስጥም እንዲሁ ከፍተኛ ጭማሪ ታይቷል። በአጠቃላይ በኦስትሪያ የሟቾች ቁጥር ማክሰኞ ከ 1000 በላይ ሆኗል።

ጣሊያን ውስጥም ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ በሃያ አራት ሰዓታት ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ወደ 22,000 ደርሰዋል። አዲስ የተጣለውን ገደብ በመቃወም ሰኞ አመሻሽ ላይ የተቃውሞ ሰልፎች በጣሊያን ተካሂደዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ምን አለ?

ከቢቢሲ ወርልድ ጋር ቆይታ ያደረጉት ያደረጉት ዶ/ር ሃሪስ "በመላው አውሮፓ የከፋ እና አስደንጋጭ በሆነ መልኩ በቫይረሱ የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ጭማሪ እያየን ነው" ብለዋል።

ከቀደመው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር በየቀኑ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአንድ ሦስተኛ ሲጨምር የሚመዘገበው የሞት መጠን በ40 በመቶ ከፍ ብሏል።

"የሆስፒታሎችን አቅም በተሻለ መንገድ ማስተዳደር ቢቻልም በበርካታ አገራት የሚገኙ ሆስፒታሎች አልጋዎች በፍጥነት እየተያዙ ነው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

"በተወሰኑ የአውሮፓ አገራት ውስጥ የተጣሉ አዳዲስ ገደቦች ውጤታማነት የሚታወቀው በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ነው" ብለዋል።

ሩሲያ ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው ስፍራዎች የአፍና አፍኝጫ መሸፈኛዎችን ማድረግን አስገዳጅ አድርጋለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሩሲያ ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው ስፍራዎች የአፍና አፍኝጫ መሸፈኛዎችን ማድረግን አስገዳጅ አድርጋለች።

ሩሲያ ከዛሬ ጀምሮ ሰዎች በሚበዙባቸው እንደ ትራንስፖርት አገልግሎት፣ ታክሲ እና አሳንሰር ያሉ ቦታዎች ላይ የአፍና አፍኝጫ መሸፈኛዎችን ማድረግን አስገዳጅ አድርጋለች።

የፈረንሳይ መንግሥት በፓሪስ እና በሌሎች ከተሞች ውስጥ ቀድሞ የተጣሉትን እገዳዎች ማራዘምን ጨምሮ ጥብቅ እርምጃዎችን በመተግበር ላይ እየተወያየ ነው።

ጣሊያን ካለፈው አርብ ጀምሮ ምግብና እና መጠጥ ቤቶች፣ የስፖርት መዝወተሪያ ስፍራዎች ና ሲኒማዎች ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ መዘጋታቸውን በመቃወም በቱሪን ሰልፍ ያደረጉ ዜጎች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው ፖሊስ በሰልፈኞች ላይ አስለቃሽ ጭስ ለመተኮስ ተገዷል።